14.1.1 በግራ እና በቀኝ ቬንትሪክል መካከል የሚገኘው ግድግዳ ወይም የቬንትሪከል ሴፕተም መሽንቆር (VSD)
በጤነኛ ልብ አፈጣጠር ወቅት በግራ እና በቀኝ ቬንትሪክሎች መካከል የሚገኘው የቬንትሪክል ግድግዳ የቬንትሪክል ሴፕተም (ventricular) septum ተብሎ ይጠራል። የቬንትሪክል ሴፕተም መፈጠር የሚጀምረው በፅንሱ እደሜ ከአራተኛው ሳምንት ጀምሮ ሲሆን በስምንተኛው ሳምንት ላይ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል። የቬንትሪከል ሴፕተም የሚሰራው ከሁለት የተለያዩ ክፍሎች ነው።
በታችኛው ክፍል የሚገኘው እና አብዛኛውን የቬንትሪክል ሴፕተም የሚሸፍነው ክፍል ከቬንትሪክል ጡንቻ የሚሰራ ሲሆን ከላይ በኩል የሚገኘው የቬንትሪክል ሴፕተም ክፍል ደግሞ የሚሰራው ከኢንዶካርዲያል ኮሺን በሚነሳው ስስ ሽፋን ክፍል ነው። የታችኛው የቬንትሪክል ሴፕተም ክፍል ወደ ላይ በማደግ ከላይኛው የቬንትሪክል ሴፕተም ክፍል ጋር ሳይገናኝ ለጥቂት ጊዜ በሁለቱ የቬንትሪክል ክፍሎች መካከል ክፍተት በመፍጠር ደም ማሳለፊያ በር እንዲፈጠር ያደርጋል። በሂደትም ከታች የሚመጣው ከጡንቻ የሚሰራው የቬንትሪክል ሴፕተም ክፍል ከላይ በኩል ከሚመጣው ስስ ሽፋን መሰል የቬንትሪክል ሴፕተም ክፍል ጋር በመገናኘት ወይም በመጋጠም በግራ እና በቀኝ ቬንትሪክሎች መካከል የነበረው ክፍትት እንዲዘጋ ያደርጋል። የቬንትሪክል ሴፕተም በተገቢው መልኩ ሳይስራ ሲቀር ወይም ከላይ እና ከታች በኩል የሚገኙት የቬንትሪክል ክፍሎች በሚገባ መገናኘት ወይም መጋጠም በማይችሉበት ወቅት የቬንትሪክል ሴፕተም መሸንቆር ወይም በግራ እና በቀኝ ቬንትሪክሎች መክከል በሚገኘው ግድግዳ ላይ ቀዳዳ ወይም ክፍተት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
ለቬንትሪክል ሴፕተም መሽንቆር መፈጠር አጋላጭ ከሆኑ ሆኔታዎች መካከል በዘረ መል ወይም በክሮሞዞሞች ላይ ከሚፈጠር ለውጥ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (የዳውን ሲንድሮም / Downs syndrome፣ ኢድዋርድ ሲንድሮም / Edward syndrome እና ፓቱ ሲንድሮም / patau syndrome) ፣ በእርግዝና ወቅት በእናትየው ላይ የሚፈጠሩ የተለያዩ ኢንፌክሽኖች እንዲሁም በእናትየው ላይ የሚከሰት የስኳር በሽታ ፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት እና ሲጋራ ማጤስ ዋንኞቹ ሆኔታዎች ናቸው።
በልብ እና በደም ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት ከሚፈጠሩ የጤና ችግሮች መካከል በተደጋጋሚ የሚከሰተው የጤና ችግር የቬንትሪክል ሴፕተም መሽንቆር / VSD ነው።
በግራ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገኝው የግፊት መጠን በቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ ከሚገኘው ግፊት የበለጠ ስለሆነ የቬንትሪክል ግድግዳ መሸንቆር በሚያጋጥምበት ወቅት ከግራ ቬንትሪክል ወደ ቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የተጣራ ደም በቀኝ ቬንትሪክል ከሚገባው ያልተጣራ ደም ጋር በመደባለቅ በፑልሞናሪ አርተሪ በኩል ወደ ሳንባ የሚረጭ ይሆናል። ህጻኑ በሚወለድበት ወቅት ወደ ሳንባ የሚደረሰው የተጣራ እና ያልተጣራ ድብልቅ ደም በሳንባ ተጣርቶ በግራ ቬንትሪክል በኩል ወደ ሰሰውነት ክፍሎች ስለሚረጭ በደም ውስጥ የሚገኘው የኦክስጂን መጠን ጤነኛ ይሆናል። ስለሆነም ህጻኑ በሚወለድበት ወቅት የቆዳ ቀለም ለውጥ ወይም ሌሎች ምልክቶችን ላያሳይ ይችላል።
በቬንትሪክል ሴፕተም መሽንቆር የተጠቁ ህጻናት እንደተወለዱ ምንም ዓይነት ምልክቶችን ላያሳዩ ይችላሉ። የቬንትሪከል ሴፕተም መሽንቆር መጠኑ ትንሽ ከሆነ በጊዜ ሂደት በራሱ ለዘጋ ይችላል። ትልቅ የቬንትሪክል ሴፕተም መሽንቆር ግን በሂደት የልብ ድካም በሽታ እንዲፈጠር ሊያደርግ ስለሚችል በቀዶ ጥገና ሽንቆሩን መዝጋት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
የቬንትሪክል ሴፕተም መሽንቆር ሳይታከም ለረጅም ግዜ በሚቆየበት ወቅት የልብ ምት መዛባት ፣ የልብ ድካም ፣ በፑልሞናሪ አርተሪ ውስጥ የሚገኘው የደም ግፊት መጠን መጨመር ፣ የኢዝንመንገር የኢስሲንድሮም (Eisenmenger syndrome)፣ በተደጋጋሚ በልብ የወስጥ ክፍሎች ውስጥ የሚፈጠር ኢንፌክሽን እና የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር በትክክል መዘጋት አለመቻል እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።
