19.3 በውጭኛው እና በውስጠኛው ፔሪካርዲየሞች መካከል የልብን ተግባር የሚገድብ ከፍተኛ መጠን ያለው የፈሳሽ መጠራቀም (Cardiac tamponade)
ይህ ዓይነት የፒሪካርዲየም የልብ የጤና ችግር በዋነኝነት የሚፈጠረው ከላይ በተገለጸው መልኩ በሴረስ ፔሪካርዲየም ላይ ብግነት ወይም ኢንፌክሽን በሚያስከትሉ እንዲሁም በሌሎች በሴረስ ፔሪካርዲየም መካከል በሚገኘው ክፍተት ውስጥ የፈሳሽ መጠራቀም እንዲፈጠር በሚያደርጉ ሆኔታዎች የተነሳ ነው።
በሴረስ ፔሪካርዲየሞች መካከል በሚገኘው ክፍተት ውስጥ የሚኖረው የፈሳሽ መጠን በከፍተኛ ደረጃ በሚጨምርበት ወቅት በልብ ጡንቻ ላይ በሚያሳድረው ጫና የቀኝ አትሪየም እና የቅኝ ቬንትሪክል በተገቢው መጠን በመለጠጥ ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚመጣውን ደም መቀበል እንዳይችሉ ያደርጋል። ይህም ሆኔታ ወደ ቬንትሪክል የሚገባው የደም መጠን ፣ በያንድ አንዱ የልብ መኮማተር ወቅት ከልብ የሚረጨው የደም መጠን እና በአርተሪ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚኖረው የደም ግፊት መጠን እንዲቀንስ እንዲሁም በደም መልስ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚኘው የደም መጠን መጨመር እንዲከሰት ያደርጋል።
በዚህ ዓይነት በፔሪካርዲየም ላይ ከሚፈጠር የጤና ችግር ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የአተነፋፈስ ፍጥነት መጠን መጨመር ፣ የትንፋሽ ማጠር ፣ የደም ግፊት መጠን መቀነስ ፣ አየር ወደ ውስጥ ወይም ወደ ሳንባ እየገባ የደም ግፊት መጠን በሚለካበት ወቅት አስቀድሞ ከነበረው የደም ግፊት መጠን ከ 10 ሚሊሜትር ኦፍ ሚርኮሪ በላይ በሆነ መጠን መቀነስ (pulsus paradoxus) ፣ የልብ ምት ድምጽን መስማት አለመቻል ፣ በጉበት ውስጥ የሚከማቸው የፈሳሽ መጠን መጨመር እና በእግር ላይ የሚፈጠር ዕብጠት ዋንኞቹ ናቸው።
በኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ የተለያየ መጠን ያለው የ አር ሞገድ (R wave) የሚታይ ሲሆን በኢኮካርዲዮግራም ምርመራ ደግሞ በውጭኛው እና በውስጠኛው የሴረስ ፔሪካርዲየሞች መካከል በሚገኘው ከፍተት ውስጥ የሚኖረው የፈሳሽ መጠን መጨመር ፣ የቀኝ እትሪየም እና ቬንትሪክል ግድግዳ መጨፍለቅ ወይም መሰርጎድ ሊታይ ይችላል።
በሴረስ ፔሪካርዲየሞች መካከል የሚገኘውን ፈሳሽ የተለያዩ የህክምና መንገዶችን በመጠቀም እና በአስቸኳይ በማከም ሞትን ጨምሮ የከፋ የልብ የጤና ችግሮችን የመከሰት ዕድል መቀነስ ይቻላል። በፔሪካርዲየሞች መካከል በሚገኘው ክፍተት ውስጥ የተከማቸውን ፈሳሽ ቀድቶ በማስወገድ ፣ ፈሳሽ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ እንዲሁም የደም መልስ የደም ቧንቧዎች እንዲሰፉ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን በማስወገድ ወይም ባለመጠቀም ፣ በደም ቧንቧ በኩል የሚሰጡ ፈሳሾችን በመጠቀም የሰውነት ፈሳሽ መጠን እንዲጨምር በማድረግ በያአንደ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ከልብ የሚረጨውን የደም መጠን መጨመር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ለልብ ሽፋን ብግነት ወይም ኢንፌክሽን መንስሄ የሆነውን ሆኔታ በሚገባ መለየት ፣ በፔሪካርዲየም ክፍተት ውስጥ የሚገኘው የፈሳሽ መጠን እንዲጨምር ሊያደርጉ የሚችሉ የጤና ችግሮችን መቆጣጠር እንዲሁም ከሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት ጋር በተገናኘ በፔሪካርዲየም ላይ ብግነት እንዲፈጠር የሚያደርጉ የጤና ችግሮችን መለየት እና ማከም በጣም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።