17. በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Valvular heart diseases)
በልብ የውስጠኛ ክፍል እና በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች በተደጋጋሚ ሊከሰቱ የሚችሉ እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮች ናቸው። በልብ ውስጥ በሚከሰት ኢንፌክሽን ወይም ብግነት ፣ በልብ በሮች ላይ የሚፈጠር የካልሲየም ክምችት ፣ በልብ በሮች ላይ የሚፈጠር የዳነ ቁስለት እንዲሁም በልብ በር አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠር ጉድለት ወይም እክል እና የመሳሰሉት ሆኔታዎች በልብ የውስጥ ክፍል በተለይም በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን የሚያስከትሉ ሆኔታዎች ናችው።
በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች በልብ በላይኛው ከፍል ወይም በአትሪየም እና በታችኛው የልብ ክፍል ወይም በቬንትሪክል እንዲሁም በልብ እና ከልብ ጋር በተገናኙ የደም ቧንቧዎች መካከል የሚኖረው የደም ፍሰት እንዲዘጋ ወይም በተቃራኒ አቅጣጫ እንዲፈስ ሊያደርጉ ይችላሉ። በተጨማሪም የልብን የደም መርጨት ተግባር በማስተጓጓል በልብ ላይ የሥራ ጫና እንዲፈጠር እና ቀስ በቀስም ወደ ልብ ድካም ደረጃ ላይ ሊያደርስ የሚችል የልብ የጤና ችግር እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።
ጤነኛ የልብ በሮች በሚከፈቱበት ወቅት የደም ፍሰት በአንድ አቅጣጫ እንዲቀላጠፍ የሚያደርጉ ሲሆን የልብ በሮች በተገቢው መጠን መከፈት በማይችሉበት ወቅት የሚፈጠር የደም ፍሰትን የሚገድብ የልብ በር የጤና ችግር የልብ በር መጥበብ (stenosis)) ተብሎ ይጠራል። በልብ በር መጥበብ የተነሳ በልብ ውስጥ እና ከልብ ጋር ተገናኝተው ደም ክልብ እንዲወጣ በሚያደርጉ የደም ቧንቧዎች ውስጥ በሚኖረው የደም ፍሰት ላይ ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት የደም ፍሰቱን በጠበበው የልብ በር በኩል አሳልፎ ደም ወደሚፈልግበት አቅጣጫ እንዲጓዝ ለማድረግ የልብ ጡንቻ በከፍተኛ ጉልበት ለመኮማተር እና ደምን ለመርጨት የበለጠ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል። ይህም ሆኔታ ቀስ በቀስ በልብ ጡንቻ ላይ በሚያሳድረው ተጽህኖ የተነሳ የልብ ግድግዳ በከፍተኛ መጠን እንዲወፍር (concentric hypertrophy) እና ቀጥሎም የልብ የመሥራት ወይም ደምን የመቀበል እና የመርጨት አቅም እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል።
ከልብ በሮች በትክክል አለመከፈት ወይም የልብ በሮች መጥበብ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለወጦች ደረጃ እና ዓይነት በልብ በር ላይ በደረሰው ጉዳት እና የጥበት መጠን ላይ የሚወሰን ሲሆን የልብ በሮች በከፍተኛ ደረጃ በሚጠቡበት ወቅት በሽተኛው የሚያሳየው ምልክት እና የስሜት ለውጥ የከፋ ይሆናል።
የልብ በሮች ደም በአንድ አቅጣጫ እንዲያልፍ ካደረጉ በኋላ በሚዘጉበት ወቅት ደግሞ በልብ በሮች ውስጥ ያለፈው ደም ወደነበረበት የልብ ክፍል ተመልሶ እንዳይፈስ ይከላከላሉ። የልብ በሮች በትክክል መዘጋት በማይችሉበት ወቅት የሚከሰት እና ደም በተቃራኒ አቅጣጫ በመፍሰስ ተመልሶ ወደነበረበት የልብ ክፍል ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ የልብ በሮች የጤና ችግር የልብ በሮች በትክክል አለመዘጋት (regurgitation) ተብሎ ይጠራል።
የልብ በሮች በትክክል በማይዘጉበት ወቅት በልብ በሮች በኩል አልፎ ወደ ፊት ወይም ወደሚቀጥለው የልብ ወይም የደም ቧንቧ ክፍል ውስጥ ያልፈው ደም ወደነበረበት የልብ ወይም የደም ቧንቧ ክፍል ውስጥ ተመልሶ የሚገባ ይሆናል።
ለምሳሌ፡ ደም ከቀኝ አትሪየም በትራይካስፒድ በር በኩል ወደ ቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ ከገባ በኋላ የትራካስፒድ በር የሚዘጋ ይሆናል። ይህም የትራካስፒድ በር መዘጋት ቬንትሪክል በሚኮማተርበት ወቅት በቬንትሪክል ውስጥ የሚገኘው ደም ተመልሶ ወደ አትሪየም ውስጥ እንዳይገባ ያግዳል።
የትራይካስፒድ በር በትክክል መዘጋት በማይችልበት ወቅት ቬንትሪክል በሚኮማተርበት ወቅት የትራይካስፒድ በር የደምን ከቬንትሪክል ወደ አትሪየም መመለስ መገደብ ሰለማይችል ደም ከቬንትሪክል በመወጣት ወደ አትሪየም የሚመለስ ይሆናል። ይህም ሆኔታ ቬንትሪክል በሚኮማተርበት ወቅት ባልተገባ መልኩ በተቃራኒ አቅጣጫ ከቬንትሪክል ወደ አትሪየም የሚገባው የደም መጠን እንዲጨምር እንዲሁም ቬንትሪክል በሚለጠጥበት ወቅት ደግሞ ከአትሪየም ተመልሶ ወደ ቬንትሪክል ውሰጥ የሚገባው የደም መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።
ከአትሪየም ወደ ቬንትሪክል የሚገባውን ከፍተኛ መጠን ያለው ደም ለመቀበል እና ለሰውነት በቂ በሆነ መጠን ከቬንትሪክል ገፍቶ ለመርጨት ይችል ዘንድ የቬንትሪክል ግድግዳ እየወፈረ እና አየሰፋ (eccentric hypertrophy) መምጣት ይጀምራል። በሂደትም ከቬንትሪክል ወደ አትሪየም ውስጥ የሚገባው ደም ተመልሶ ወደ ቬንትሪክል ውሰጥ በሚገባበት ወቅት በቬንትሪክል ውሰጥ የሚኖረው የደም መጠን በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ስለሚያደርግ ቀስ በቀስ የቬንትሪክል ጡንቻ እየተለጠጠ በመምጣት የቬንትሪክል መስፋት አየጨመረ ይመጣል።
የልብ በሮች በትክክል መዘጋት አለመቻል ቀስ በቀስ ወይም በድንገት ሊከሰት ይችላል። በልብ በሮች ላይ የሚፈጠር ኢንፌክሽን ወይም የልብ በሮች በትክክል እንዲዘጉ እና እንዲከፈቱ በሚያደርጉ ኮርዲኒዎች፣ ቲንዲኖች እና ጡንቻዎች ላይ የሚፈጠር ጉዳት በፍጥነት የሚከሰት የልብ በሮች በትክክል መዘጋት አለመቻል እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። በፍጥነት የሚከሰት የልብ በሮች በትክክል መዘጋት አለመቻል በሚፈጠርበት ወቅት ልብ የተፈጠረውን ሆኔታ ለማስተካከል በቂ ግዜ ስለማያገኝ በድንገት የሚከሰት የልብ ድካም ወይም የልብ የመሥራት አቅም መቀነስ ሊያስከትል ይችላል።
አንድ አንድ ግዜ በልብ በሮች ላይ የሚከሰት ጉዳት የልብ በሮች መጥበብ እና የልብ በሮች በትክክል አለመዘጋት በአንድ ላይ ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም በልብ በሮች ላይ የሚከሰት ጉዳት አብዛኛውን ግዜ የሚያስከትለው የበሮች መጥበብ ወይም የልብ በሮች በትክክል አለመሥራት ወይም መዘጋት አለመቻል ነው። በጎሮሮ ውስጥ ከሚከሰት የስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በስውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት የተነሳ በልብ በሮች ላይ በሚከሰት ቁስለት ወይም ጉዳት (rheumatic heart diseases) ወይም ከእድሜ መግፋት ጋር በተገናኘ በልብ በሮች ላይ የሚፈጠር የካልሲየም ክምችት ወይም ከ እድሜ መግፋት ጋር በተጋኘ በልብ በሮች ላይ የሚከሰት ለውጥ የልብ በሮች መጥበብ (Stenosis) የጤና ችግር እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ። በተጨማሪም በልብ የውስጥ ክፍሎች ውስጥ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች ወይም ብግነቶች በልብ በሮች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት የተነሳ የልብ በር መጥበብ ወይም የልብ በር በትክክል አለመዘጋት የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የልብ በሮች ፣ በልብ አፈጣጠር ወቅት የሚፈጠር የልብ የጤና ችግር ያለባቸው ወይም የሰው ሰራሽ የልብ በሮች የተገጠሙላቸው ሰዎች በልብ ውስጥ ወይም በልብ በሮች ላይ ለሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች የተጋለጡ ናቸው። ስለሆነም በልብ ውስጥ እና በልብ በሮች ላይ ሊከሰት የሚችል ኢንፌክሽንን ለመከላከል የሚረዱ ጸረ ባክቲሪያ መድኃኒቶችን መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
በልብ በሮች ላይ የሚፈጠር የጤና ችግር በልብ አፈጣጠር ወቅት በሚፈጠር የጤና ችግር ወይም ህጻኑ ከተወለደ በኋላ በልብ በሮች ላይ በሚከሰቱ የተለያዩ ጉዳቶች የተነሳ ሊፈጠር ይችላል። ህጻኑ ከተወለደ በኋላ በልብ በሮች ላይ የሚከሰት የጤና ችግር ከሚያስከትሉ ሆኔታዎች በተለይም በታዳጊ ሀገራት ውስጥ የሚከሰተው በጎሮሮ ላይ ከሚፈጠር የስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በልብ በሮች ላይ የሚከሰት ጉዳት ዋንኛው ነው።
ህጻናት ልጆች በተለይም በእድሜያቸው በ 5 እና 13 ዓመት መካከል የሚገኙ ልጆች በስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ነው። የስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ በጎሮሮ ላይ ኢንፌክሽን በሚያስክትልበት ወቅት የሰውነት ሙቀት መጨመር ፣ የጎሮሮ ህመም ፣ የራስ ምታታ ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና በሰውነት በተለይም በአንገት እና በጀርባ አካባቢ የሚወጣ ሽፍታ እና ምግብ በሚመገቡበት ወቅር በጎሮሮ ላይ የሚሰማ ህምም ሊያስከትል ይችላል።
የስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን በሚከሰትበት ወቅት ሰውነት የስትሪፕቶኮካል ባክትሪያን ከሰውነት ለማስወገድ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖችን ያመርታል። ምንም አንኳን አነዚህ የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች በዋናነት የሚመረቱት በሽታ አምጭ የሆነውን ባካቲሪያ ከሰውነት ለማስወገድ ቢሆንም በበሽታ አምጭ ባክቲሪያ ባህድ አካል እና በሰውነት ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ሴሎች መካከል በሚኖረው መመሳሰል የተነሳ በሽታ አምጭ የሆነውን ባካቲሪያ ከሰውነት ለማስወገድ የሚመረተው የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲን በልብ በሮች ፣ በአጥንት መገጣጣሚያ እንዲሁም በእንጎል ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ሴሎችን የሚያጠቃ ይሆናል።
በጎሮሮ ወስጥ የሚፈጠር የስትሪፕቶኮካል ባከቲሪያ ኢንፌክሽንን ተከትሎ የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት በአንጎል ፣ በአጥንት መገጣጠሚያዎች ፣ በልብ ክፍሎች እና በቆዳ ላይ በሚያሰከትለው ጉዳት የተነሳ የሚፈጠር የጤና ችግር ከሰትሪፐቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኝ በበሸታ መከላኪያ ፕሮቲኖች የተነሳ የሚፈጠር የጤና ችግር (rheumatic fever) ተብሎ ይጠራል።
ከስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች በልብ ጡንቻ እና በልብ በሮች ላይ በሚያስከትሉት ጉዳት የተነሳ የሚፈጠር የልብ የጤና ችግር ከስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሚከሰት የልብ የጤና ችግር (rheumatic heart diseases) ተብሎ ይጠራል። ከስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን በተደጋጋሚ መከሰት ጋር በተገናኘ በሚመረቱ የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች የተነሳ በልብ ከፍሎች በተለይም በልብ በሮች ላይ የሚከሰት የጤና ችግር በታዳጊ ሀገራት ውስጥ በሚገኙ ልጆች እና አዋቂዎች ላይ ዋንኛ በልብ በሮች ላይ ጉዳት የሚያስከትል የጤና ችግር ነው።