20.3. የደም ግፊት መጠን መጨመርን መቆጣጠር (Treatment of hypertension)
መንሰሄው የማይታወቅ የደም ግፊት መጠን መጨመር በሽታን መቆጣጠር እንጂ ማዳን አይቻልም። የደም ግፊት መጠን መጨመርን ለመቆጣጠር የሚረዱ መድኃኒቶችን መቼ መጀመር ያስፈልጋል? በምን ዓይነት መድኃኒቶች ወይም በስንት ዓይነት መድኃኒቶች ህክምናው መጀመር አለበት ? ወይም ከህክምና በኋላ የሚጠበቀው የደም ግፊት መጠን ምን ያህል መሆን አለበት? ለሚሉት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ በተለያዩ ሆኔታዎች ላይ የሚወሰን ይሆናል። ከእነዚህም ሆኔታዎች ውስጥ የበሽተኛው እድሜ ፣ የደም ግፊት መጠን መጨመር ደረጃ ፣ በበሽተኛው ላይ የሚገኙ ሌሎች የጤና ችግሮች ፣ በሽተኛው ለሌሎች በሽታዎች የሚጠቀማቸው መድኃኒቶች እንዲሁም እርግዝና እና ጡት ማጥባት ዋንኞቹ ናቸው።
በ 2017 የአሜሪካን የልብ ማህበር ለደም ግፊት መጠን መጨመር በሽታ ህክምና ባወጣው መመሪያ መሰረት የደም ግፊት መጠን መጨመርን ለማከም በቅድሚያ መድረግ ያለበት ጉዳይ የህይወት እና የአኗኗር ሆኔታን ማሻሻል ነው። የሴስቶሊክ የደም ግፊት መጠን ከ 120 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኮሪ (> 120 mm Hg ) በላይ ወይም የዲያሰቶሊክ የደም ግፊት መጠን ከ 80 ሚሊ ሜትር አፍ ሜርኮሪ ( > 80 mm Hg ) በላይ በሚሆንበት ወቅት የህይወት እና የአኗኗር ሆኔታን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ይሆናል።
የደም ግፊት መጠን መጨመርን ለመቆጣጠር የሚረዱ መድኃኒቶችን ምቼ እና በምን አይነት መድኃኒት መጀመር እንዳለበት ከላይ እንደተገለፀው በተለያዩ ሆኔታዎች ላይ የሚወሰን ቢሆንም በሰፊው ጥቅም ላይ ውሎ የሚገኘው መመሪያ የሚከተለው ነው።
- የሲስቶሊክ የደ ግፊት መጠን ከ 130 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኮሪ ( ≥ 130 mm Hg) በላይ ወይም የዲያስቶሊክ የደም ግፊት መጠን ከ 80 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኮሪ (≥ 80 mm Hg) በላይ በሆነበት ሆኔታ እና ከሚከተሉት የጤና ችግሮች ውስጥ አንድ ወይም ከአንድ በላይ በተከሰተበት ሆኔታ ውስጥ የመድኃኒት ህክምና መጀመር አሰፈላጊ ሊሆን ይቸላል።
– ወደ ልብ ሴሎች የሚደረሰው የኦክስጂን መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ የጤና ችግር (IHD) ፣ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ በሚፈጠር ጉዳት የተነሳ የሚከሰት የደም ቧንቧ የጤና ችግር (PVD) ፣ የልብ ድካም በሽታ ፣ በአንጎል ውስጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ በሚከሰት ጉዳት የተነሳ በአንጎል ከፍሎች ላይ የሚፈጠር ጉዳት ወይም ስትሮክ እንዲሁም በአሥር አመት ውስጥ በደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ ከሚፈጠር የስብ ክምችት ጋር በተገናኘ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ተጋላጭነት ቀመር (10 year ASCVD risk) ከ 10 በመቶ ( ≥ 10% ) በላይ መሆን ናቸው።
በአሥር አመት ውስጥ በደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ ከሚፈጠር የስብ ክምችት ጋር በተገናኘ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ተጋላጭነት ቀመር እድሜን ፣ የስኳር በሽታን እንዲሁም ሌሎች ሆኔታዎችን በመጠቀም የሚቀመር ወይም የሚሰላ ውጤት ነው።
- የሲስቶሊክ የደም ግፊት መጠን ከ 140 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኮሪ (≥ 140 mm Hg ) በላይ መሆን ወይም የዲያስቶሊክ የደም ግፊት መጠን ከ 90 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኮሪ (≥ 90 mm Hg ) በላይ መሆን ናቸው።
ለደም ግፊት መጠን መጨመር በሽታ የሚሰጠው ህክምና ያለመድኃኒት የሚሰጥ ህክምና (የህይወት እና የኖሩ ዘይቤን በማሻሻል) ወይም መደኃኒትን በመጠቀም የሚሰጥ ህክምና ወይም በሁለቱም መንገዶች የሚሰጥ ህክምና ሊሆን ይችላል።
ለያንድ አንዱ በሽተኛ ተመራጭ የሚሆነው የህክምና ወይም የመድኃኒት ዓይነት እንደ በሽተኛው የጤንነት ሆኔታ ወይም ሌሎች ተጓደኝ የጤና ችግሮች እና በደም ግፊት መጠን መጨመረ ደረጃ ላይ የሚወሰን ይሆናል።
በተጨማሪም ከህክምና በኋላ የሚጠበቀው የደም ግፊት መጠን እንደ በሽተኛው የጤንነት ሆኔታ ፣ እድሜ ወይም ተጓዳኝ በሽታዎች ላይ የሚወስን ይሆናል። በአጠቃላይ በሚሰጠው የምክር እና / ወይም የመድኃኒት ህክምና የሚጠበቀው የደም ግፊት መጠን ከ 130 / 80 ሚሊ ሜትር ኦፍ ሜርኮሪ በታች (< 130/80 mm Hg ) እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።
ህክምናው ( የህይወት እና አኗኗር ዘይቤ ማሻሻል ወይም የመድኃኒት ህክምና ) ከተጀመረ በኋላ በየግዜው የደም ግፊት መጠንን እና ከሚወሰደው መድኃኒት ጋር በተገናኘ ሊፈጠሩ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንዲሁም ከደም ግፊት መጠን መጨመር ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን መከታተል አስፈላጊ ይሆናል።