22.2. ከስትሪፕቶኮካል የጉጉሮሮ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ የጤና ችግር (Rheumatic heart disease)
በአለም ላይ በጉሮሮ ውስጥ ኢንፌክሽን እንዲፈጠር ከሚያደርጉ የባክቴሪያ ዓይነቶች መካከል የስትሪፕቶኮካል ባክቴሪያ አንዱ እና ዋንኛው ነው። በተለይም የስትሪፐቶኮካል ባክቴሪያ ኢንፌክሽንን ለመከላከል እና ሊያደርስ የሚችለውን የጤና ጉዳት ለመቀነስ የሚረዳ ህክምና በቀላሉ ማግኘት የማይችሉ ወይም በታዳጊ ሀገራት ውሰጥ የሚኖሩ ህጻናት እና ልጆች በተደጋጋሚ ግዜ ለሚከሰት የስትሪፕቶኮካል የጉሮሮ ኢንፊክሽን ተጋልጭ ናቸው። በተደጋጋሚ የሚከሰት የጉሮሮ ስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ወይም በሚገባ ያልታከም የስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ከሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት ጋር በተገናኘ በፍጥነት ወይም በረጅም ግዜ ውስጥ ልብን ጨምሮ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ የሚፈጠር ጉዳት እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።
የስትሪፕቶኮካል ባክቴሪያ ኢንፌክሽን የጉሮሮን ክፍል ከማጥቃት በተጨማሪ ከሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት ጋር በተገናኘ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይም የተለያዩ የከፉ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል። የስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ በጉሮሮ ላይ የሚፈጥረውን ጉዳት ተከትሉ የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት ባክቴሪያውን ከሰውነት ለማስወገድ የሚያገለግሉ የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖችን ያመርታል። ይህ የስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያን ከሰውነት ለማስወገድ የሚመረት የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲን ከባክቲሪያው ጋር በሚኖራቸው መመሳሰል የተነሳ በአንጎል ፣ በልብ ፣ በአጥንት መገጣጠሚያዎች እና በቆዳ ውስጥ በሚገኙ የሰውነት ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን የሚያስከትል ይሆናል።ይህ ከስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በከፍተኛ መጠን የሚመረት የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ በሚያደረሰው ጉዳት የተነሳ በአንጎል ፣ በልብ ፣ በአጥንት መገጣጠሚያዎች እና በቆዳ ክፍሎች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ ሆኔታ ከስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚፈጠር ጉዳት (rheumatic fever (RF) ተብሎ ይጠራል።
ከስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚፈጠር ጉዳት (RF) የሚከሰተው በምድብ ኤ የስትሪፕትኮካል ባክቴርያ ( Streptococcal Group A) ዝርያ አማካኝነት ሲሆን በዚህ ዓይነት የባክቴሪያ ዝርያ የሚፈጠርን የጉሮሮ ኢንፌክሽንን ተከትሉ ሰውነት በሽታውን ለመከላከል በሚያመርታቸው የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች የተነሳ በልብ ፣ በአጥንት መገጣጠሚያ ፣ በአንጎል እና በቆዳ ላይ በሚያደርሰው ብግነት የተነሳ የሚከሰት የጤና ችግር ነው። በተለይም ስትሪፕትኮካል አይነት ኤ ባክቴርያ ዋንኛ የጉሮሮ እና የቆዳ እንፌክሽን አምጭ ህዋስ ሲሆን ከሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት ጋር በተገናኘ በኩላሊት የግሎመሩለስ ክፍል ላይ በሚያስክተለው ብግነት የተነሳ በኩላሊት ላይ ከፍተኛ ጉዳት (post streptococcal glomerulonephritis) እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
በተለያዩ በሽታ አምጭ ህዋሳት አማካኝነት የሚፈጠር ኢንፌክሽንን ለመከላከል ወይም ወደሰውነት የሚገባን ባዕድ አካል ከሰውነት ለማስወገድ የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት የሚያመርታቸው ጸረ ባክቲሪያ ወይም ጸረ ባዕድ ፕሮቲኖች የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች ወይም አንቲቦዲዎች (Antibodies) ተብለው ይጠራሉ። በጉሮሮ ውስጥ የሚከሰት የስትሪፕትኮካል አይነት ኤ ባክቴርያ ኢንፌክሽንን ተከትሎ የሚመረተው የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲን ወይም አንቲ ቦዲ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን እንደ ባክቴሪያው አካል ወይም ባህድ አካል በመቁጠር በሚያደርሰው ጉዳት በዋናነት በልብ ፣ በኩላሊት ፣ በአንጎል ፣ በአጥንት መገጣጠሚያ እና በቆዳ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።
ምንም እንኳን ከስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ የጤና ችግር በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሊያጠቃ የሚችል ቢሆንም በብዛት የሚከሰተው እድሜያቸው ከ 5 – 15 አመት የአድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ልጆች ላይ ነው። በተደጋጋሚ በስትሪፕቶኮካል የጉሮሮ ኢንፌክሽን የሚጠቁ ህጻናት በተደጋጋሚ ከሚከሰት የስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ ለሚፈጠር የልብ የጤና ችግር በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ይሆናሉ። በሰትሪፕቶኮካል አይነት ኤ ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰቱ የጉሮሮ ኢንፊክሽኖችን በተገቢው ጊዜ ውስጥ ወይም በፍጥነት ትከክለኛ መድኃኒቶችን በመጠቀም በማከም እንዲሁም ከስትሪፕቶኮካል ባክቴሪያ ጋር በተገናኘ የሚከሰት ኢንፌክሽንን እና የልብ የጤና ችግርን ለመከላከል የሚረዳ ክትባትን በመጠቀም የበሽታውንሥርጭት እና የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ ይችላል።
ክትባትን እንዲሁም በተገቢው ጊዜ ትክክለኛ መድኃኒቶችን በመጠቀም በሚሰጥ ህክምና ባደጉ ሀገራት ውሰጥ የሚከሰተውን ከስትሪፕቶኮካል ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ የጤና ችግርን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ቢቻልም አሁንም ቢሆን ኢትዮጲያን ጨምሮ በሌሎች በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ውስጥ የበሽታው ሥርጭት እና የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው። በዚህም የተነሳ በኢትዮጲያ ውስጥ ዋና የልብ በር የጤና ችግሮች መንስሄ የስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን መሆኑ ይታወቃል።
በተደጋጋሚ ከሚከሰት የስትሪፕቶኮካል የጉሮሮ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ የጤና ችግር በልብ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የተለያየ ነው። ምንም እንኳን በተደጋጋሚ ከሚከሰት የስትሪፕቶኮካል የጉሮሮ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ የጤና ችግር በዋነኝነት በልብ በሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን የሚያስከትል ቢሆንም በልብ ጡንቻ (myocarditis) እንዲሁም በልብ ሽፋን ለይ ጉዳት (pericarditis) እንዱፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
በተደጋጋሚ ከሚከሰት የስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮችን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች የተለያዩ ናቸው። ብዙሁን ጊዜ በልብ በሮች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ምንም ዓይነት ምልክቶችን ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል። ከስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ ሊከሰት የሚችል የልብ የጤና ችግር የሚያሳያቸው ምልክቶች እና ለውጦች የሚፈጠሩት በሚገባ ያልታከመ የስትሪፕቶኮካል የጉሮሮ ኢንፌክሽን ከተከሰተ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው። ከስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ለሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከልም የሰውነት ሙቀት መጠን መጨመር ወይም ትኩሳት ፣ አጠቃላይ ከፍተኛ የሆነ የህመም ስሜት (malaises ) እና በአጥንት መገጣጠሚያ ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰት ህመም ፣ እብጠት እና የመቅላት ሆኔታዎች እንዲሁም በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ሽፍታ እና ችፍታ ጥቂቶቹ ናቸው።
ከስትሪፕቶኮካል ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በሚከሰት የልብ የጤና ችግር በዋናነት የሚጠቁት የሚትራል በር ( mitral valve) እና የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር (aortic valve) ሲሆኑ አንድ አንድ ጊዜ የትራይካሰፒድ በር (tricuspid valve) ሊጠቃ ይችላል። በልብ በሮች ላይ የሚከሰተው ጉዳት የሚገለጸው ችግሩ እንደተከሰተ የሚትራል በር መዘጋት እንዳይችል እና ደም ከግራ ቬንትሪክል ወደ ግራ አትሪየም እንዲፍስ (mitral regurgitation) በማድረግ ሲሆን የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ የሚትራል በር መጥበብ ወይም መዘጋት ( mitral stenosis) እንዲፈጠር ያደርጋል።
በሽታውን ለማወቅ ከሚደረጉ ምርመራዎች መካከል በደም ናሙና ላይ በሚደረግ ምርመራ በደም ውስጥ የሚገኘው የጸረ – ስትሪፕቶላይሲን ኦ (Antistreptolysin O) የበሸታ መከላኪያ ፕሮቲን መጠን መጨመር እና ከልብ ክፍሎች ውስጥ በሚወሰድ ናሙና ላይ በሚሰራ የፓቶሎጂ ምርመራ ደግሞ የአስኮፍ አካሎች (Aschoff body) እና የአንቲስኮው ሴሎች (Anitschkow cells) በልብ ጡንቻ ውስጥ ተከማችተው የሚታዩ ይሆናል።
በስትሪፕቶኮካል ባክቴሪያ የሚፈጠር ኢንፌክሽን በሚከሰትበት ወቅት ኢንፌክሽኑን በፍጥነት በተገቢው መልኩ ማከም በጣም አስፈላጊ ይሆናል። ይህም ከስትሪፕሮኮካል ባክቲሪያ ጋር በተገናኘ የሚፈጠረውን የልብ የጤና ችግር ለመከላከል በጣም ወሳኝ ሆኔታ ነው። ስለሆነም የጎሮሮ ህመም ወይም ኢንፌክሽን በሚያጋጥምበት ወቀት የጤና ባለሞያ ማመከር እንዲሁም በጤና ባለሞያ የሚታዘዙ ጸረ ባክቴሪያ መድኃኒቶችን በታዘዘው መጠን እና ቀናት ውስጥ መውሰድ በጣም አስፈላጊ ይሆናል።
በተደጋጋሚ የጎጎሮሮ ኢንፌክሽን የሚከሰትበቸው እንዲሁም በሚተኙበት ወቅት ጤነኛ ያልሆነ ከአተነፋፈስ ጋር በተገናኘ የሚሰማ ድምፅ የሚፈጥሩ ወይም በሚተኙበት ውቅት የሚያንኮራፉ ልጆች የልብ የጤንነት ምረመራ እንዲያደረጉ ይመከራሉ።
የስትሪፕቶኮካል ባክቴርያ ኢንፌክሽንን ተከትሎ የሚፈጠረውን የጉሮሮ ጉዳት ለመቀነስ እንዲሁም የልብ የጤና ችግሮችንን ለመከላከል መድኃኒት የሚታዘዝላቸው በሽተኞች መድኃኒታቸውን በታዘዘላቸው መጠን እና ግዜ መሰረት መወስድ ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም በሽተኞች የሚታዘዝላቸውን መድኃኒት ያለማቋረጥ እንዲወስዱ እና መድኃኒታቸውን በትክክል በታዘዘው መሰረት በማይውስዱበት ወቅት ሊከሰት ስለሚችለው የከፋ የጤና ችግር አስፈላጊውን ምክር ማግኘት ይኖርባቸዋል።