Course Content
ምዕራፍ አሥራ አራት : በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች
0/16
ምዕራፍ አሥራ አምሥት : ከልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮች (Cardiac electrical system abnormalities)
0/16
ምዕራፍ አስራ ሰባት : በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Valvular heart diseases)
0/16
ምዕራፍ ሃያ አንድ : የልብ ድካምበሽታ (Heart failure )
0/1
ምዕራፍ ሃያ ሦስት : በደም ቧንቧዎች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Vascular diseases)
0/22
በልብ እና በደም ቧንቧ ሥር ዓት ክፍሎች ውስጥ ሊፈጠሪ የሚችሉ የጤና ችግሮች (Pathology of Cardiovascular System)

16.1.1.2. የሚትራል በር መዘጋት አለመቻል (Mitral regurgitation)

  የሚትራል በር ከተዘጋ በኋላ የቨ‍ኤንትሪከልን መኮማተር ተከትሎ በቬንትሪክል ውስጥ የሚገኘው ደም በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በኩል ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ይረጫል። የሚትራል በር በትክክል መዘጋት አለመቻል በሚፈጠርበት ወቅት የግራ ቬንትሪክልን መኮማተር ተከትሎ ደም ከግራ ቬንትሪክል ወደ ግራ አትሪየም ውስጥ ተመልሶ የሚገባ ይሆናል። ከሚትራል በር መዘጋት አለመቻል ጋር በተገናኘ ወደ ግራ አትሪየም ውስጥ የሚመለሰው የደም መጠን በሚትራል በር ላይ ከሚከሰተው ጉዳት በተጨማሪ ቬንትሪክል የበለጠ እንዲሰራ በሚያደርገው ሃይል (after load) ላይ የሚወስን ይሆናል። ይህም ማለት የሚትራል በር መዘጋት አለመቻል በሚፈጠርበት ወቅት ከግራ ቬንትሪክል የሚረጨውን ደም መጠን የሚገድብ ማንኛውም ሆኔታ ከግራ ከቬንትሪክል ተመልሶ ወደ ግራ አትሪየም ውስጥ የሚገባው የደም መጠን እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። 

  ወደ ግራ አትሪየም ወስጥ ገብቶ የነበረው ደም ተመልሶ ወደ ግራ ቬንትሪክል ውስጥ በሚገባበት ወቅት በግራ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም እና የግፊት መጠን  እንዲጨምር ስለሚያደርግ ቀስ በቀስ የግራ ቬንትሪክል መለጠጥን እና መስፋትን በመጨረሻም በግራ የልብ ክፍል ላይ በተፈጠረው ጉዳት የተነሳ የልብ ድካም በሽታን (left sided heart failure) የሚያስክተል ይሆናል።

    የሚትራል በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር ቀስ በቀስ ወይም በፍጥነት ሊከሰት ይችላል። በኮርዲ ቲንዲኒ (ከቬንትሪክል ላይ ከሚነሱ የፓፒላሪ ጡንቻዎች እና በሚትራል በር ተካፋቾች (cusps) መካከል የሚገኝ አገናኝ ክፍል ወይም ቲንደን ) መበጠስ ፣ በፓፒላሪ ጡንቻ ላይ የሚከሰት ጉዳት ፣ በልብ ውስጥ ከሚከሰት ኢንፌክሽን ወይም በልብ ላይ ከሚከሰት አደጋ (trauma) ጋር በተገናኝ በሚትራል በር ላይ የሚፈጠር ጉዳት ዋንኞቹ በፍጥነት የሚከሰት የሚትራል በር መዘጋት አለመቻል ሊያስከትሉ የሚችሉ ሆኔታዎች ናቸው።

     በተደጋጋሚ ከሚፈጠር ከስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት በልብ ክፍሎች ላይ በሚያደረሰው ጉዳት የተነሳ የሚከሰት የልብ የጤና ችግር (rheumatic heart diseases)  ፣ የፓፒላሪ ጡንቻ በትክክል አለመሥራት ፣ የሚትራል በር መገኘት ከሚኖርበት ትክክለኛ የልብ ክፍል ተነስቶ ወደ አትሪየም ውስጥ መግባት ፣ በልብ ውስጥ የሚከሰት ኢንፌክሽን ወይም በግነት ፣ በሚትራል በር ላይ የሚፈጠር የካልሲየም መከማቸት እንዲሁም የቬንትሪክል ግድግዳ ከሚገባው መጠን በላይ መለጠጥ የመሳሰሉት ሆኔታዎቸ‍ በረጅም ግዜ ውስጥ የሚትራል በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር አንዲከሰት ሊያደርጉ የሚችሉ ሆኔታዎች ናቸው።

   .የሚትራል በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር በሚከሰትበት ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የትንፋሽ ማጠር ፣ ተንጋለው ሲተኙ የሚባባስ የትንፋሽ ማጠር ፣ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ በተደጋጋሚ የሚከሰት ሳል ፣ በእግር ላይ እና በሆድ ውስጥ የሚፈጠር እብጠት ፣ አጠቃላይ የድካም ስሜት መሰማት እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋንኞቹ ናቸው።

    ከሚትራል በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር መከሰት ጋር በተገናኘ በአካላዊ ምርመራ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል  የልብ ሞግድ ወይም ትርታ በጤነኛ ሰው ላይ ከሚገኝበት የደረት ክፍል ላይ ወደ ታች እና ወደ ጎን ዝቅ ብሎ መገኘት (displaced apical impulse) ፣  በደረት የግራ ክፍል ላይ ወደ ብሽሽት እና አንገት የሚሰራጭ ጤነኛ ያለሆነ የልብ ምት ድምጽ (holosystolic murmur) ፣ ዓይነት ሦስት ተጨማሪ የልብ ምት ድምጽ ( S3) እንዲሁም በአንገት አካባቢ የተገታተሩ የደም መልስ ቧንቧዎች (distended veins) መታየት ሊከሰት ይችላል። 

   የሚትራል በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር መከስቱን ለማወቅ ከሚደረጉ የምርመራ መንገዶች መካከል የኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ የግራ ቬንትሪክል ግድግዳ መወፈርን ወይም የግራ አትሪየም መስፋትን ሊያሳይ ይችላል። የደረት የራጅ ምርመራ የልብ መጠን መጨመርን በተለይም የግራ ቬንትሪክል በመጠን መጨመርን ሊያሳይ ይችላል። የኢኮካርዲዮግራም ምርምራ ደግሞ ከኮርዲ ቲንዲኒ መበጠስ ወይም በፓፒላሪ ጡንቻ  ላይ በሚከሰት ጉዳት የተነሳ የሚትራል በር ወደ አትሪየም ውስጥ መግባትን ሊያሳይ ይችላል።

  ቀጭን ቧንቧ መሰል ማሳሪያ ወይም ካቴተር በአንገት ወይም በብሽሽት አካባቢ በሚገኙ ትልልቅ የደም ቧንቧዎች በኩል በማስገባት በልብ ውስጥ የሚገኙ ክፍሎችን ለማየት እና ጤነኛ ያልሆኑ ሆኔታዎችን ለማስተካከል የሚረዳ ምርመራ ወይም የካርዲያክ ካቴተራይዜሽን ምርመራ (cardiac catheterization) ማድረግ ከሁሉም ከላይ ከተገለጹት የምርመራ መንገዶች በበለጠ ሆኔታ በሚትራል በር ላይ እና በአጠቃላይ በልብ ውስጥ የሚከሰት ለውጥን ለመለየት እና አሰፈላጊ በሚሆንበት ወቅትም ህክምና ለመስጠት የሚረዳ የምርመራ መንገድ ነው።

የሚትራል በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግርን የተለያዩ መድኃኒቶችን በመጠቀም ወይም በቀዶ ጥገና ማከም ይቻላል።

   ከቬንትሪክል የሚረጨውን የደም ፍስት የሚገድብ ሃይል ወይም ቬንትሪክል በሚኮማተርበት ወቅት ደም ወደ ሰውነት እንዳይረጭ የሚያደርግ ግድብትን መጠን የሚቀንሱ  ወይም የአርተሪ የደም ቧንቧዎች እንዲሰፉ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን በመጠቀም ከግራ ቬንትሪክል ተመልሶ ወደ ግራ አትሪየም የሚገባውን የደም መጠን መቀነስ ይቻላል። ከቬንትሪክል የሚረጨውን የደም ፍስት የሚገድብ ሃይልን ወይም ቬንትሪክል በሚኮማተርበት ወቅት ደም ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እንዳይረጭ የሚያደርግ ግድብትን መጠን ለመቀነስ ከሚረዱ መድኃኒቶች መካከል የአንጂኦቲኒሲን ሁለት ተቀባዩችን የሚዘጉ መድኃኒቶች (ARBs) ወይም አንጂአቲንሲን አንድን ወደ አንጂኦቲንሲን ሁለት የሚቀየረውን ኢንዛይም ተግባር የሚገድቡ መድኃኒቶችን (ACEi) ወይም የአርተሪ ቧንቧዎች እንደስፉ የሚያደርጉ መድኃኒቶች እና ፈሳሽ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ መድኃኒቶች ዋንኞቹ ናቸው።

  ከላይ በተጠቀሱት የህክምና መንገዶች ከሚትራል በር መዘጋት አለመቻል ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልከቶችን እና ለውጦችን በሚገባ መቆጣጠር በማይቻልበት ወቅት ወይም በሌሎች የህክምና መንገዶች አጥጋቢ ምላሽ በማይገኝበት ወቅት ወይም በያንድ አንዱ መኮማተር ወቅት ከቬንትሪክል የሚረጨው የደም መጠን በከፍተኛ ደረጃ በሚቀንስበት ወቅት ወይም የግራ ቬንትሪክል ከመጠን በላይ በሚለጠጥበት ወቅት  በቀዶ ጥገና ህክምና በሚትራል በር ላይ የተፈጠረውን ጉዳት ማስተካከል ወይም የሚትራል በርን በሌላ አዲስ ሰው ሰራሽ በር መተካት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።