19.1 በፍጥነት የሚከሰት የፔሪካርዲየም ብግነት (Acute pericarditis)
በፍጥነት የሚከሰት የልብ ሽፋን ወይም የፔሪካርዲየም ብግነት የጤና ችግር በዋናነት የሚፈጠረው በሴረስ ፒሪካርዲየም ላይ ኢንፌክሽን ወይም ብግነት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ሆኔታዎች ነው። በሴረስ ፔሪካርዲየም ላይ ኢንፌክሸን እንዲፈጠር ከሚያደርጉ ሆኔታዎች መካከል በተለያዩ የቫይረስ ( የኮክሳኬ ቫይረስ) ፣ የባክቴሪያ ( የስትሪፕቶኮካል ፣ የስታፊሎኮከስ ፣ የሳንባ ነቀርሳ ) ፣ የፈንገስ እና የሌሎቸ ተዋሲያን ኢንፊክሽኖች ዋንኞቹ ናቸው። በተጨማሪም በሴረስ ፔሪካርዲየም ላይ ብግነት እንዲፈጠር ከሚያደርጉ ሆኔታዎች መካከል በልብ ወይም በፔሪካርዲየም ላይ የሚከሰት አደጋ ፣ የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች ፣ ለጨረር መጋለጥ ፣ የልብ የቀዶ ጥገና ህክምና ማድረግ ፣ ከኩላሊት መድከም ጋር በተገናኘ በደም ውስጥ የሚገኘው የዩሪያ ናይትሮጂን በከፍተኛ መጠን መጨመር ፣ የሴረስ ፔሪካርዲየም በሰውነት የበሽታ መከላኪያ መጠቃት ፣ ወደ ልብ ሴሎች ከሚደርሰው የደም መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የከፋ የልብ የጤና ችግር እና የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ግድግዳ መሰንጠቅ ዋንኞቹ ናቸው ።
በፔሪካርዲየም ላይ የሚፈጠረውን ኢንፌክሽን ወይም ብግነት በውጭኛው እና በውስጠኛው ፒሪካርዲየሞች መካከል በሚገኘው ክፍተት ውስጥ የሚኖረው የፈሳሽ መጠን መጨመር እንዲፈጠር ሊያደረግ ይችላል። ይህም ፈሳሽ ልብ በሚገባው መልኩ እንዳይለጠጥ እና ደምን እንዳይቀበል ሊያገድ ይችላል። በውጭኛው እና በውስጠኛው ፒሪካርዲየሞች መካከል በሚገኘው ክፍተት ውስጥ የሚፈጠረው የፈሳሽ መጠን መጨመር የአትሪየምን እና የቬንተሪክልን የመለጠጥ እና ደም የመቀበል አቅምን በመቀነስ ፣ በደም መልስ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚኖረው የደም እና የግፊት መጠን እንዲጨምር ፣ ወደ ልብ ተመልሶ የሚገባው የደም መጠን እንዲቀንስ እንዲሁም በያንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ክልብ የሚረጨው የደም መጠን እንዲቀንስ በማድረግ በአርተሪ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚኖረው የግፊት መጠን እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል።
በፍጥነት የሚከሰት የፔሪካርዲየም ብግነት መከሰትን ተከትሎ ከሚታዩ ምልክቶች እና ለውጦች መካክል የሰውነት ሙቀት መጨመር ወይም ትኩሳት ፣ የአተነፋፈስ ፍጥነት መጠን መጨመር ፣ በአተነፋፈስ ወቅት በደረት ላይ የሚሰማ የህመም ስሜት ፣ በሽተኛው ተነጋሉ በሚተኛበት ወቅት የሚጨምር እና ወደ ፊት አዘንብሎ በሚቀመጥበት ወይም ወደ ፊት ጎንበስ በሚልበት ወቅት የሚቀንስ የደረት ህመም ፣ የትንፋሽ ማጠር ፣ የደም ግፊት በከፍተኛ መጠን መቀነስ ፣ በአንገት አካባቢ በሚገኙ የደም መልስ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚኖረው የፈሳሽ መጠን መጨመር እና መገታተር ፣ አየር ወደ ውስጥ ወይም ወደ ሳንባ እየገባ የደም ግፊት መጠን በሚለካበት ወቅት አስቀድሞ ከነበረው የደም ግፊት መጠን ላይ ከ 10 ሚሊሜትር ኦፍ ሚርኮሪ በላይ በሆነ መጠን መቀነስ (pulsus paradoxus) ፣ በአካላዊ ምርመራ የልብ ምት ደምጽን መስማት አለመቻል ፣ በጉበት ውስጥ የሚከማቸው የፈሳሽ መጠን መጨመር እና የእግር ዕብጠት ሊከሰት ይችላል።
በኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ የተለያየ መጠን ያለው የ አተ ሞገድ (R waves) የሚታይ ሲሆን በኢኮካርዲዮግራም ምርመራ ደግሞ በውጭኛው እና በውስጠኛው የሴረስ ፔሪካርዲየሞች መካከል በሚገኘው ከፍተት ውስጥ የሚኖረው የፈሳሽ መጠን መጨመር ፣ የቀኝ ቬንትሪክል ግድግዳ መጨፍለቅ ወይም መሰርጎድ ሊታይ ይችላል።
በፍጥነት የሚከሰት የፔሪካርዲየም ብግነት ብዙሁን ግዜ ያለምንም ህክምና በራሱ ሊድን የሚችል ሲሆን የሰውነት ሙቀትን እና በደረት ላይ የሚፈጠረውን ህመም ለመቀነስ የሚረዱ መድኃኒቶችን እንዲሁም የሰወነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓትን ተግባር የሚገድቡ መድኃኒቶችን መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ለበሽታው መንስሄ በሆነው ሆኒታ ላይ በመመሰረት የጸረ – ባክቲሪያ መድኃኒቶችን ፣ የጸረ – የሳንባ ነቀረሳ መድኃኒቶችን ወይም ጸረ – ካንሰር መድኃኒቶችን ወይም የዲያሊሲስ ህክምና መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
በሴረስ ፒሪካርዲየሞች መካከል የሚገኘው ፈሳሽ ከመጠን በላይ በሚጨምረበት ወቅት የተከማቸውን ፈሳሽ በፍጥነት ማስወገድ አስፈላጊ ይሆናል። በተጨማሪም በፍጥነት የሚከሰት የፔሪካሪዲየም ብግነት ወይም ኢንፌክሸእን መንስሄ የሆነውን የጤና ችግር በሚገባ ማከም አስፈላጊ ይሆናል። አንድ አንድ ግዜም ጉዳት የደረሰበትን የልብ ሽፋን ወይም ፔሪካርዲየም በተለያዩ የህክምና መንገዶች በማከም አጠጋቢ ውጤት ማግኘት በማይቻልበት ወቅት የቀዶ ጥገና ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
በውጭኛው እና በውስጠኛው የሴረስ ፒሪካርዲየሞች መካከል በሚገኘው ክፍተት ውስጥ የሚገኘው የፈሳሽ መጠን መጨመር (pericardial effusion) ፣ በረጅም ጊዜ ወሰጥ የፔሪካርዲየም መወፈር ወይም መጠንከር የሚያሰከትል የፔሪካርዲየም ብግነት (Constrictive pericarditis) እንዲሁም በውጭኛው እና በውስጠኛው ፔሪካርዲየሞች መካከል የልብን ተግባር የሚገድብ ከፍተኛ መጠን ያለው የፈሳሽ መጠራቀም (cardiac tamponade) ዋንኞቹ በልብ ሸፋን ላይ በፍጥነት የሚከሰት ብግነትን ወይም ኢንፌክሽንን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የከፉ የልብ ጤና ችግሮች ናቸው።