15.3.1.3. የአትሪየም ፊብሪሌሽን (Atrial fibrillation)
የአትሪየም ፊብሪሌሽን የሚፈጠረው በአትሪየም ውስጥ ከሚገኙ ሴሎች ውስጥ በሚነሱ እና በተለያየ ተቃራኒ አቅጣጫዎች በሚፈሱ በጣም ፈጣን የሆኑ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴዎች የተነሳ ነው።
እነዚህ በተለያየ የአትሪየም ክፍል ውስጥ በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴዎች የእትሪየም ጡንቻ መኮማተር እንዲችል ማድረግ ስለማይችሉ በኤሌክትሮካርዲዩግራም ምርመራ ውጤት ላይ የ ፒ (P) ሞገድ በግልፅ ሊታይ አይችልም ። በምትኩም መሥመር የሚመስሉ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴዎች (f waves) የሚታዩ ይሆናል።
በአትሪም ውስጥ በተለያየ ክፍል ውስጥ የሚፈጠሩ እና በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴዎች እርስ በእርስ የሚጠፋፉ ስለሆነ እና ወደ ቬንትሪክል የሚያልፈው የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ ስለሆነ በአትሪየም መኮማተር እና በቬንትርክል መኮማተር መካከል የሚኖረው ግንኙነት የተዘበራረቀ ይሆናል። በዚህም ምክንያት በተከታታይ በሚታዩ የአር ( R ) ሞገዶች መካከል የሚኖረው ርቀት የተለያየ ይሆናል።
በአትሪየም ውስጥ የሚፈጠረውን የልብ ምት መዛባት በተገቢ መንገድ በፍጥነት በማሰተካከል ወደ ቬንትሪክል ውስጥ እንዳያልፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ተገቢ ባልሆነ መልኩ በአትሪየም ውስጥ የሚፈጠር የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ በአትሪዩቬንትሪኪዩላር ኖድ በኩል ወደ ቬንትሪክል ውስጥ በማለፍ እና የቬንትሪክልን የመኮማተር እና የመለጠጥ አቅም በመቀነስ ለከፋ የጤና ችግር እንዲሁም በፍጥነት ለሚከሰት የሞት አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። ስለሆነም በአተሪየም ውስጥ የሚከሰቱ የልብ ምት መዛባት ችግሮችን በተለይም የአትሪየም ፊብሪሌሽን የልብ መዛባት የጤና ችግርን በአፋጣኝ ማከም በጣም አስፈላጊ ይሆናል።
የአትሪየም ፊብሪሌሽን በሚፈጠርበት ወቅት የአተሪየም ጡነቻ በሚገባ በመኮማተር ደምን ወደ ቬንትሪክል ወሰጥ ማሰገባት ስለማይችል በአትሪየም ወሰጥ የደም መረጋት (atrial clots) እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። ከአትሪየም ፊብሪሌሽን ጋር በተገናኘ በአትሪየም ውሰጥ የሚፈጠር የደም መርጋት በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በኩል ክልብ በመውጣት እና በሌሎች የደም ቧንቧዎች ውስጥ በመሰንቀር እና የደም ፍሰትን በመዘጋት በአንጎል ክፍሎች እና በልብ ላይ የከፋ የጤና ችግር ሊያሰከትል ይችላል።
በአትሪየም ውስጥ የሚከሰቱ የልብ መዛባት የጤና ችግሮችን ለማከም የሚረዳው መንገድ በአትሪዩቬንትሪኪዩላር ኖድ ውስጥ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴን የሚገድቡ መድኃኒቶችን መጠቀም ዋንኛው ነው። የኢትሪዩቬንትሪኪዩላር ኖድን የኤሌከትሪክ እንቅስቃሴ በመገደብ በአትሪየም ውስጥ የሚከሰቱ የልብ ምት መዛባቶች ወደ ቬንትሪክል ውስጥ በማለፍ የከፋ የጤና ችግር እንዳያደርሱ ከሚረዱ መድኃኒቶች መካከል በአትሪዩቬንትሪክዩላር ኖድ ላይ የሚገኙ የቤታ አንድ በሮችን የሚዘጉ መድኃኒቶች (beta 1 blockers) ፣ የካልሲየም በሮችን የሚዘጉ መድኃኒቶች (calcium channel blockers) እና የዲጂታሊስ (digitalis) መድኃኒቶች ዋንኞቹ ናቸው ።

በተጨማሪም ከአትሪየም ፊብሪሌሽን ጋር በተገናኘ ሊፈጠር የሚቸለውን የደም መረጋት ለመከላከል የሚረዱ ደም ማቅጠኛ መደኃኒቶችን መጠቀም እንዲሁም የልብ ምት መዛባቱን የተለያዩ መደኃኒቶችን በመጠቀም መቆጣጠር በማቻልበት ወቅት ደግሞ የልብ ምትን ለማሰተካከል የሚረዳውን መሳሪያ (defibrillator) መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።