Course Content
ምዕራፍ አሥራ አራት : በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች
0/16
ምዕራፍ አሥራ አምሥት : ከልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮች (Cardiac electrical system abnormalities)
0/16
ምዕራፍ አስራ ሰባት : በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Valvular heart diseases)
0/16
ምዕራፍ ሃያ አንድ : የልብ ድካምበሽታ (Heart failure )
0/1
ምዕራፍ ሃያ ሦስት : በደም ቧንቧዎች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Vascular diseases)
0/22
በልብ እና በደም ቧንቧ ሥር ዓት ክፍሎች ውስጥ ሊፈጠሪ የሚችሉ የጤና ችግሮች (Pathology of Cardiovascular System)

23.2.  የደም ቧንቧዎች ብግነት (vasculitis) 

  በተለያየ ምክንያት በሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሴሎች ወይም ከበሽታ መከላኪያ ሴሎች በሚመረቱ የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች የተነሳ በደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ የሚፈጠር መቆጣት ወይም ቁስለት የደም ቧንቧ ብግነት (Vasculitis) ተብሎ ይጠራል።  በደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ በሚፈጠረው ቁስለት ወይም ብግነት የተነሳ የደም ቧንቧ ግድግዳ ላይ መሳሳት ፣ መለጠጥ ፣ መሰርጎድ እንዲሁም መጥበብ እና መዘጋት ሊከሰት ይችላል። የደም ቧንቧ ግድግዳ ላይ የሚደርስ ብግነት ወይም ቁስለት በአርተሪ ፣ በቬን ወይም በካፕላሪስ የደም ቧንቧዎች ላይ ሊከሰት ይችላል። 

  በደም ቧንቧዎች ላይ የሚደርሰው ቁስለት ወይም ብግነት በሁሉም የእድሜ ክልል ላይ በሚገኙ ስዎች ላይ ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም አንድ አንድ የደም ቧንቧ ቁስለት ወይም ብግነት በሽታ ዓይነቶች በተለየ ሆኔታ በተወሰነ የእድሜ ክልል ላይ በሚገኙ ሰዎች ላይ ሲከሰቱ ይስተዋላል። 

   ብዙሁን ግዜ በደም ቧንቧዎች ላይ ቁስለት ወይም ብግነት የሚፈጠርበት ምክንያት በትክክል አይታወቅም። በቫይረስ እና በሌሎች ህዋሳት የሚፈጠር ኢንፌክሽን ፣ የተለያዩ መድኃኒቶችን መጠቀም ፣ በሰውነት ውሰጥ የሚፈጠሩ የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች እንዲሁም ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ በሰውነት ውስጥ የሚመረቱ የበሽታ መከላኪያ ሴሎች እና የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች በደም ቧንቧዎች ላይ ጉዳት በማድረስ የደም ቧንቧ ግድግዳ ቁስለትን ወይም ብግነትን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ይታመናል።

   በደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ የሚፈጠር ብግነት በጤና ላይ ከቀላል እስከ ከፍተኛ የጤና ጉዳት የሚያስከትል ችግር ነው። ለረጅም ጊዜ የቆየ የደም ቧንቧ ግድግዳ ብግነት የደም ቧንቧ ግድግዳ ላይ በሚያደርሰው ጉዳት የተነሳ የደም ቧንቧ ግድግዳ መለጠጥ ፣  መሳሳት ፣ መሰርጎድ እና መሽንቆር ወይም መቀደድ ወይም መፈንዳት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። በአንድ አንድ የደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ የሚፈጠር ብግነት የደም ቧንቧዎች እንዲጠቡ በማድረግ እና የደም ፍሰትን በማቋረጥ ወይም በመገደብ በሰውነት ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

    በደም ቧንቧዎች ላይ ከሚፈጠር ብግነት ወይም ቁስለት ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች ጉዳት በደረሰበት የደም ቧንቧ ዓይነት እና መጠን እንዲሁም ጉዳት በደረሰበት የሰውነተ ክፍል ክፍል እና መጠን መሰረት የተለያዩ ናቸው። 

ለምሳሌ ፡ ደምን ወደ ቆዳ የሚወስዱ የደም ቧንቧዎች በብግነት መጠቃትን ተከትሎ በቆዳ ላይ የሚታይ ሽፍታ ፣ ደምን ወደ ነርቮች የሚወስዱ የደም ቧንቧዎች ላይ የሚፈጠር ብግነት በቆዳ ላይ የሚሰማ ስሜትን ማጣት እና የሰውነት ክፍሎች መታዘዝ አለመቻል ፣ መድከም እና መሰለል ፣ በአንጎል ውስጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ በሚፈጠር ብግነት የስትሮክ መከሰት ፣ ወደ ልብ ደም የሚያደርሱ የደም ቧንቧዎችን የሚያጠቃ ብግነት ወደ ልብ የሚደርሰው የኦክስጂን እና የንጥረ ምግቦች መጠን እንዲቀንስ በማድረግ በልብ ጡንቻ ላይ የሚፈጠር ጉዳት ፣ በኩላሊት ውስጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ የሚፈጠር ብግነት ወይም ቁስለት የኩላሊት መድከም እና ሌሎንችንም የጤና ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። 

   በአጠቃላይ በደም ቧንቧ ግድግዳ ላይ ከሚፈጠር ቁስለት ወይም ብግነት ጋር በተገናኘ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ከሚፈጠሩ ጉዳቶች የተነሳ የሰውነት ሙቀት መጨመር ወይም ትኩሳት ፣ የሰውነት ከብደት መጠን መቀነስ ፣ የድካም ስሜት መሰማት ፣ የራስ ምታት ፣ በድንገት የሚከሰት በመንጋጋ ላይ የሚከሰት ህምም ፣ የዓይን የማየት ችሎታ መቀነስ ወይም ማየት አለመቻል እንዲሁም በድንገት በእጅ እና በእግር ላይ ከእንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚፈጠር ድንገተኛ የህመም ስሜት በብዛት የሚታዩ ምልክቶች እና ለውጦች  ናቸው።