14.2.3. የትራይካስፒድ በር በትክክል አለመፍጠር (Tricuspid Atresia / TA)
በአትሪየም እና በቬንትሪክል መካከል ከሚገኙት የልብ በሮች መካከል በቀኝ አትሪየም እና በቀኝ ቬንትሪክል መካከል የሚገኘው በር የትራይካስፒድ በር (Tricuspid valve) ተብሎ ይጠራል። በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት ሊፈጠሩ ከሚችሉ የጤና ችግሮች መካከል የትራይካስፒድ በር በተገቢው መልኩ አለመፈጠር (TA) አንዱ ነው። የትራይካስፒድ በር ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በትክክል መፈጠር በማይችልበት ወቅት ደም ከቀኝ አትሪየም ወደ ቀኝ ቬንትሪክል መግባት አይችልም። የትራይካስፒድ በር በትክክል አለመፈጠር የጤና ችግር ጋር በተያያዥነት ሊከሰቱ ከሚችሉ ሌሎች የጤና ችግሮች መካከል የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር (ASD) ፣ የቬንትሪክል ሴፕተም መሽንቆር (VSD)፣ የቀኝ ቬንትሪክል መጠን መቀነስ እንዲሁም የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር መጥበብ እና የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር በትክክል አለመዘጋት አለመቻል ዋንኞቹ ናቸው።
ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ተሰበስቡ ወደ ቀኝ አትሪየም ውስጥ የሚገባው ያለተጣራ ደም ወደ ቀኝ ቬንትሪክል ውሰጥ በሚፈለገው መጠን መግባት በማይችልበት ወቅት በቀኝ አትሪየም ውስጥ የሚኖረው የደም እና የግፊት መጠን የሚጨምር ይሆናል። በዚህም ምክንያት በቀኝ አትሪየም ወስጥ የሚፈጠረው የግፊት መጠን በግራ አትሪየም ውስጥ ከሚፈጠረው ግፊት በበለጠ መጠን ስለሚጨምር ያልተጣራው ደም ከቀኝ አትሪየም በፎራመን ኦቫለ (foramen ovale) በኩል በቀላሉ ወደ ግራ አትሪየም ከዚያም ወደ ግራ ቬንትሪክል በማለፍ እና በግራ ቬንትሪክል ውስጥ ከሚገኘው የተጣራ ደም ጋር በመደባለቅ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚረጭ ይሆናል።
የትራይካስፒድ በር በትክክል አለመፈጠር የጤና ችግር በሚፈጠርበት ወቅት በቀኝ አትሪየም ውስጥ የሚገኘው ያልተጣራ ደም በግራ አትሪየም ውስጥ ከሚገኘው የተጣራ ደም ጋር ተደባልቆ በግራ ቬንትሪክል በኩል ስለሚወጣ በደም ውስጥ የሚገኝው የኦክስጂን መጠን ዝቅተኛ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ህጻኑ እንደተወለደ የቆዳ ለውጥ እና ሌሎች ምልክቶችን የሚያሳይ ይሆናል ። እነዚህ ህጻናት አስቸኳይ የሆነ የልብ የቀዶ ህክምና ካልተደረገላቸው በስተቀር በህይወት የመቆየት እድላቸው በጣም አነስተኛ ነው።
ህጻኑ ከተወለደ በኋላ የህጻኑን የጤንነት ሆኔታ ለማስተካከል እንዲሁም የሚከሰቱ ምልክቶችን እና ለውጦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የፕሮስታግላንዲን ሆርሞን መድኃኒትን ፣ የልብ ጡንቻ መኮማተር እንዲጨምር የሚያደርጉ መድኃኒቶችን ፣ ፈሳሽ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን እንዲሁም ኦክስጂን በሚገባው መጠን መስጠት አስፈላጊ ይሆናል። በተጨማሪም በቀዶ ጥገና ህክምና የተፈጠረውን የጤና ችግር ማስተካከል አስፈላጊ ይሆናል።