14.1.2 በግራ እና በቀኝ አትሪየም መካከል የሚገኘው ግድግዳ ወይም የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር (ASD)
በግራ እና በቀኝ አትሪየም መካከል የሚገኘው ግድግዳ ወይም የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር ችግር ሌላኛው ከቬንትሪክል ሴፕተም መሽንቆር ቀጥሎ በብዛት የሚከሰት በልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠር የጤና ችግር ነው። የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር እንዲፈጠር ሊያደርጉ ከሚችሉ ሆኔታዎች መካከል በዘረ መል ወይም ክሮሞዞም ላይ ከሚፈጠር ለውጥ የተነሳ የሚፈጠሩየጤናችግሮች (የዳውን ሲንድሮም) እንዲሁም በእናትየው በእርግዝና ወቅት የሚወሰድ የአልኮል መጠጥ (alcohol fetal syndrome) ዋንኞቹ ናቸው።
ህጻኑ ከተወለደ በኋላ በግራ አትሪየም ውስጥ የሚፈጠረው የግፊት መጠን በቀኝ አትሪየም ውሰጥ ከሚፈጠረው የግፊት መጠን ስለሚበልጥ በግራ እና በቀኝ አትሪየም መካከል የሚገኘው ግድግዳ ወይም የአትሪየም ሴፕተም ላይ መሸንቆር (ASD) በሚፈጠርበት ወቅት ደም ከግራ አትሪየም ወደ ቀኝ አትሪየም ውሰጥ የሚገባ ይሆናል። ከግራ አትሪየም የሚመጣው የተጣራ ደም እና በቀኝ አትሪየም ውስጥ የሚገኘው ያልተጣራ ደም ወደ ቀኝ ቬንትሪክል ከገባ በኃላ በፑልሞናሪ አርተሪ በኩል ወደ ሳንባ የሚረጭ ይሆናል። ወደ ሳንባ የተረጨው እና በሳንባ የተጣራው ደም ወደ ግራ አትሪየም ከዚያም ወደ ግራ ቬንትሪክል ከገባ በ ኃላ በትልቁ ደም ቅዳ በኩል ወደ ሰውነት ክፍሎች የሚረጭ ይሆናል። ስለሆነም በደም ውሰጥ የሚኖረው የኦክሰጂን መጠን ጤነኛ ስለሚሆን ህጻኑ በሚወለድበት ወቅት የቆዳ ቀለም ለወጥ ወይም ሌሎች የበሽታው ምልክቶች የሚታዩበት አይሆንም።
በግራ እና በቀኝ አትሪየም መካከል የሚገኘው ግድግዳ ወይም የአትሪየም ሴፕተም የተሰራው ከሁለት አይነት የሴፕተም አይነቶች ነው። እነዚህም ሴፕተም ፕሪሚየም ( septum primum እና ሴፕተም ሰኮንደም ( septum secundum) የሚባሉ ናቸው። ሴፕተም ፕሪሚየም ከሴፕተም ሲከንዶም ቀድሞ የሚሰራ እና በአብዛኛው በታችኛው የአትሪየም ሴፕተምን ክፍል የሚሰራ የግድግዳ ክፍል ሲሆን ፕሪሚየም ሴኮንደም ደግሞ ከፕሪሚየም ሴፕተም ቀጥሉ የሚሰራ እና በዋናነት የላይኛውን የአትሪየም ሴፕተም ክፍል የሚሰራ ወይም የሚሸፍን ክፍል ነው። እነዚህ ሁለት ክፍሎች በትከከል በመጋጠም የ አትሪየም ሴፕተምን የሚፈጥሩ ይሆናል።
የአትሪየም ሴፕተምን ከሚሰሩት የሴፕተም ፕሪሚየም እና የሴፕተም ሲኮንደም አፈጣጠር ሂደት ላይ በሚፈጠር እክል ወይም ጉድለት የተነሳ ሁለት በግራ እና በቀኝ አትሪየም መካከል የሚገኘው ግድግዳ መሽንቆር ዓይነቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
በሴፕተም ስኮንደም ላይ በሚፈጠር እክል የተነሳ የሚከሰት የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር (Ostium secundum atrial septal defect / ASD I) ፡ ይህ በሴፕተም ሴኮንደም አፈጣጠር ሂደት ወቅተ በሚከሰት እክል የተነሳ የሚፈጠር የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር በተደጋጋሚ የሚከሰት የመሸንቆር ዓይነት ሲሆን ይህ የጤና ችግር የሚከሰተው በልብ ክፍሉች አፈጣጠር ወቅት በላይኛው የአትሪየም ሴፕተም ክፍል ላይ ሴፕተም ሰኮንደም ከሴፕተም ፕሪሚየም ጋር በሚገባ መገናኘት ወይም መጋጠም ሳይችል ሲቀር ወይም በሴፕተም ሲኮንደም ማጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት በአትሪየም ሴፕተም መካከለኛ ወይም የላይኛው ክፍል ላይ መሸንቆር እንዲፈጠር ያደርጋል።
በሴፕተም ሲኮንደም ላይ በሚፈጠር እክል የተነሳ የሚከሰት የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር መጠን በጣም ትንሽ ከሆነ ህጻናቱ እስከ አዋቂነት የእድሜ ክልል ድረስ ከበሽታው ጋር በተገናኘ ምልክቶችን ላያሳዩ ይችላሉ።

ምስል 13 በግራ እና በቀኝ አትሪየም መካል የሚገኘው የልብ ግድግዳ መሸንቆር / ASD
በሴፕተም ፕሪሚየም ላይ በሚፈጠር እክል የተነሳ የሚከሰት የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር (Ostium primum atrial septal defect / ASD II) ፡ ይህ ዓይነት የአትሪየም ሴፕተም መሸንቆር የጤና ችግር የሚከሰተው የሴፕተም ፕሪሚየም በአትሪም እና በቬንትሪክል መገናኛ ላይ ከሚገኘው የልብ ክፍል ወይም ከኢንዶካርዲያል ኮሺን ጋር በተገቢው መልኩ ሳይገናኝ ሲቀር እና በግራ እና በቀኝ አትሪየም መካከል ግንኙነት ሲፈጠር ነው።
በአትሪየም እና በቬንትሪክል መካከል የሚገኘው እና የልብ በሮችን ጨምሮ የታችኛው የአትሪየም እና የላይኛው የቪንትሪክል ሴፕተም ክፍሎችን የሚሰራው የልብ ክፍል ኢንዶካርዲያል ኮሺን ( endocardial cushion) ተብሎ ይጠራል። በሴፕተም ፕሪሚየም ላይ በሚፈጠር እክል የተነሳ የሚከሰት የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር የሚከሰተው በታችኛው የአትሪየም ሴፕተም ክፍል ላይ ነው።
ይህ ዓይነቱ የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር ከላይኛው የቬንትሪክል ሴፕተም ክፍል አለመፈጠር እንዲሁም በአትሪየም እና በቬንትሪክል መካከል በሚገኙ በሮች በትክክል አለመፈጠር የተነሳ ከሚፈጠሩ የጤና ችግሮች ጋር በተያያዘ ሊከሰት ይችላሉ።

በአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር መፈጠር የተነሳ ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች በአትሪየም ሴፕተም ላይ በተፈጠረው የመሸንቆር ዓይነት እና መጠን ወይም በተፈጠረው መሽንቆር በኩል በሚያልፈው የደም መጠን ላይ የሚወሰን ይሆናል። የተፈጠረው መሽንቆር በመጠን እነስተኛ በሚሆንበት ወቅት ምንም ዓይነት ምልክት እና ለውጥ ሊከሰት የማይችል ሲሆን የመሸንቆር መጠኑ ትልቅ በሚሆንበት ወቅት ግን ከልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ።
የአትሪየም ሴፕተም መሽንቆር መጠን ትንሽ በሚሆንበት ወቅት ያለምንም ህክምና በራሱ ሊደፈን ወይም ሊዘጋ ይችላል። የሽንቆር መጠን ትልቅ በሚሆንበት ወይም ከሽንቆሩ ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶችን እና ለውጦችን በተለያዩ የህክምና መንገዶች መቆጣጠር በማይቻልበት ወቅት በቀዶ ጥገና ህክምና ሽንቆሮን መድፈን ወይም መዝጋት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
አንድ አንድ ግዜ በፅንሱ ዕድገት ወቅት ደምን ከቀኝ አትሪየም ወደ ግራ አተሪም ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው የፎራመን ኦቫለ ( foramen ovale) መሻገሪያ ህጻኑ ከተወለደ በኋላም እንደተከፈተ በሚቆይበት ወይም በማይዘጋበት ወቅት በልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት አፍጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠር የጤና ችግር እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።