14.1.6. የፑልሞናሪ አርተሪ በር መጥበብ (Pulmonary stenosis)
የፑልሞናሪ አርተሪ በር ወይም የፑልሞናሪ በር መጥበብ ሌላው በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠር የጤና ችግር ሲሆን መንስሄው በትክክል የሚታወቅ አይደለም። የፑልሞናሪ በር መጥበብ በሚፈጠርበት ወቅት ከቀኝ ቬንትሪክል የሚረጨው የደም ዝውውር የሚዘጋ ይሆናል። በዚህም በቀኝ የልብ ክፍል በተለይም በቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ የሚኖረው የግፊት መጠን በከፍተኛ መጠን የሚጨምር ይሆናል። ይህን ከፍተኛ ግፊት ለመቋቋምም የቀኝ ቬንትሪክል ግድግዳ ከሚገባው መጠን በላይ የሚወፍር ይሆናል።
ከፑልሞናሪ አርተሪ በር መጥበብ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ ምልክቶች እና ለውጦች ዓይነት እና ደረጃ በፑልሞናሪ አርተሪ በር ላይ በሚፈጠረው የጥበት መጠን ላይ የሚወስን ሲሆን በኢኮካርዲዮግራፊ ምርመራ የተከሰተወን የጤና ችግር በትክክል መለየት ይቻላል። ወደ ልብ ክፍሎች ከገባ በኃላ የሚነፋ ቀጭን ቧንቧ መስል መሳሪያ ወይም ካቴተር በፑልሞናሪ በር ውስጥ በማሳለፍ (transcatheter dilatation) ወይም በቀዶ ጥገና ህክምና የጠበበውን የፑልሞናሪ በር እንዲሰፋ ወይም እንዲከፈት በማድረግ ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶችን እና ለውጦችን መቆጣጠር ወይም በሽታውን ማከም ይቻላል።