17.1.1.1. የሚትራል በር መጥበብ (Mitral stenosis)
የሚትራል በር መጥበብ በሚከሰትበት ወቅት የግራ አትሪየም በሚኮማተርበት ወቅት ደም ከግራ አትሪየም በመውጣት ወደ ግራ ቬንትሪክል ውስጥ በሚፈለገው መጠን እንዳያልፍ ያደርጋል። ስለሆነም በግራ አትሪየም ውስጥ የሚኖረው የደም መጠን እና የግፊት መጠን አየጨመረ ይመጣል።
የሚትራል በር እየጠበበ ሲመጣ በጠበበው የሚትራል በር በኩል በቂ ደም ለማሳለፍ የግራ አትሪየም ጡንቻ የበለጠ ስለሚሰራ የግራ አተሪየም ግድግዳ እየወፈረ እና እየተለጠጠ መምጣት ይጀምራል። የሚትራል በር በጣም አየጠበበ በሚመጣበት ወቅት ደግሞ በግራ አትሪየም ውስጥ የሚገኘው የደም መጠን እና የግፊት መጠን የበለጠ አየጨመረ ይመጣል ፣ በግራ አትሪየም ወሰጥ የሚፈጠረውን የግፊት መጠን መጨመር ተከትሎ በፑልሞናሪ ቬን ውስጥ የሚኖረው የግፊት መጠን ይጨምራል ፣ በፑልሞናሪ ቬን ወሰጥ የሚፈጠረው ከፍተኛ የግፊት መጠን በሳንባ ውሰጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ አልፎ በፑልሞናሪ አርተሪ ውስጥ የሚገኘው የግፊት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል ፣ በፑልሞናሪ አርተሪ ውስጥ የሚጨምረውን የግፊት መጠን በመቋቋም ደምን ወደ ሳንባ ለመረጨት ይችል ዘንድ የቀኝ ቬንትሪክል ግድግዳ ውፍረት እየጨመረ ይመጣል ፣ በመጨረሻም በቀኝ በኩል የሚገኘው የልብ ክፍል ደም ወደ ሳንባ ለመርጨት አለመቻል ወይም የቀኝ የልብ ክፍል መድከም (right sided heart failure) ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል።
በተጨማሪም በፑልሞናሪ ቬን ቀጥሎም በፑልሞናሪ አርተሪ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚፈጠረው የፈሳሽ እና የግፊት መጠን እየጨመረ በሚመጣበት ወቅት ፈሳሽ ከደም ቧንቧዎች በመውጣት በሳንባ ውስጥ የሚከማች እና በፍጥነት የሞት አደጋን በሚያስከትል ደረጃ የከፋ የጤና ችግር እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
የሚትራል በር በዋናነት የሚፈጠረው ከስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በሚትራል በር ላይ በሚፈጠር ጉዳት የተነሳ ሲሆን አንድ አንድ ግዜ በልብ አፈጣጠር ሂደት ወቅት ከሚፈጠር ጉደለት ወይም ጉዳት የተነሳ የሚትራል በር መጥበብ ሊከሰት ይችላል።
የሚትራል በር መጥበብ ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በብዛት የሚከሰት የልብ የጤና ችግር ነው።
ከሚትራል በር መጥበብ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶች እና የስሜት ለውጦች መነሻ ደም ከግራ አትሪየም ወደ ግራ ቬንትሪክል ማለፍ አለመቻሉን ተከትሎ ወደ ፑልሞናሪ የደም ቧንቧዎች ወይም ሳንባ በሚመለሰው እና በቀኝ የልብ ክፍል ላይ በሚያሳድረው ተጽህኖ የተነሳ ነው።
ከሚትራል በር መጥበብ ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የትንፋሽ ማጠር ፣ በተደጋጋሚ ማሳል ፣ ተንጋለው በሚተኙበት ወቅት የሚነሳ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ የማፈን እና የማሳል ስሜት ፣ አጠቃላይ የድካም ስሜት መሰማት ፣ የሰውነት ጡንቻ በከፍተኛ መጠን መቀነስ ወይም የጡነቻ መከሳት ፣ ደም የቀላቀለበት አክታ እና የመሳሰሉት ምልከቶች እና ለውጦች ፈሳሽ በሳንባ እና በፑልሞናሪ የደም ቧንቧዎች ውስጥ መከማቸተ የተነሳ የሚፈጠሩ ምልክቶች ናቸው።
በሚትራል በር መጥበብ የተነሳ በቀኝ የልብ ክፍል ደምን የመርጨት አቅም በሚቀንስበት ደረጃ ላይ በሚደረስበት ወቅት ወይም በግራ የልብ ክፍል ውስጥ የተከሰተው የጤና ችግር ወደ ቀኝ የልብ ክፍል ውስጥ በማለፍ የቀኝ የልብ ክፍል ሥራ ወይም ተግባር ላይ ጫና በሚፈጠርበት ወቅት በታችኛው የሰውነት ክፍል ላይ የሚከሰት የሰውነት ዕብጠት ፣ በጉበት ውስጥ በሚከማቸው ፈሳሽ የተነሳ የጉበት መጠን መጨመር እንዲሁም በሆድ እቃ ሽፋን ውስጥ ከሚፈጠረው የፈሳሽ መጠራቀም የተነሳ የሆድ መጠን መጨመር የሚከሰት ይሆናል።
በግራ አትሪየም ውስጥ በሚፈጠረው የደም እና የግፊት መጠን መጨመር የተነሳ የግራ አትሪየም ግድግዳ በከፍተኛ ሆኔታ ይወፍራል እንደገናም ይለጠጣል ወይም ይሰፋል። ይህም ሆኔታ በአትሪየም ግድግዳ ላይ የሚኖረው የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ አንዲዛባ እና የልብ ምት መዛባት ወይም የእትሪየም ፊብሪሌሽን (atrial fibrillation) እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
የአትሪየም ፌብሪሌሽን ወይም ደካማ እና የተዘበራረቀ ወይም የተዛባ የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ በአትሪየም ግድግዳ ላይ በሚያልፍበት ወቅት የአትሪየም ጡንቻን የመኮማተር አቅም ስለሚቀንስ በአትሪየም ውስጥ የሚገኘው ደም ተገፍቶ ከመውጣት ይልቅ በአትሪየም ውስጥ የደም መርጋት እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህም የረጋ ደም እየተሰባበረ ወደ ቀኝ ቬንትሪክል ከዚያም በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በኩል አልፎ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በተለይም በአንጎል ውስጥ በሚገኙ ትንንሽ የደም ቧንቧዎች ውስጥ በመሰንቀር እና የደም ፍስትን በማስተጓጎል በአንጎል ክፍሎች ወስጥ የሚፈጠር ጉዳት ወይም ስትሮክ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
የሚትራል በር መጥበብ በሚከሰትበት ወቅት በአካልዊ ምርመራ ከሚታዩ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የልብ ምት መዛባት ፣ በሳንባ ውስጥ ፈሳሽ መከማቸቱን የሚያመለክቱ ድምጾች (pulmonary rales) ፣ ደም ከአትሪየም ወደ ቬንትሪክል በጠበበው የሚትራል በር በኩል ሲያልፍ የሚሰማ ጤነኛ ያለሆነ የልብ ምት ድምጽ (diastolic rumble) የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።
የሚትራል በር መጥበብ መከሰቱን ለማወቅ ከሚረዱ ምርመራዎች መካከል ፡
የኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ – የግራ አትሪየም እና የቀኝ ቬንትሪክል ግድግዳ መወፈርን ፣ የልብ ምት መዛባትን እንዲሁም የአትሪየም ፊብሬሌሽን መከሰቱን ሊያሳይ ይችላል።
የደረት ራጅ ምረመራ – የግራ አትሪየም መጠን መጨመሩን እና በፑልሞናሪ የደም ቧንቧዎች ላይ ለውጥ መከሰቱን ሊያሳይ ይችላል።
በኢኮካርዲዮግራም ምርመራ – የሚትራል በርን ተግባር እና መጠንን መለካት ይቻላል ፣ የግራ አትሪየም ግድግዳ መወፈሩን መለየት ይቻላል።
በሚትሪል በር መጥበብ የተነሳ የሚከሰት የልብ የጤና ችግር በሁለት መንገድ ሊታከም ይችላል። አንደኛው መንገድ ከቀዶ ጥገና ህክምና ውጭ የሚሰጥ ህክምና ሲሆን ሁለተኛው የህክምና መንገድ ደግሞ የቀዶ ጥገና ህክምና ነው።
በምግብ መልክ የሚወሰደውን የጨው መጠን መቀነስ ፣ ፈሳሽ ከሰውነት አንዲወገድ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን መጠቀም ፣ በግራ አትሪየም ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን የደም መርጋት ለመከላከል የሚረዱ የደም ማቅጠኛ መድኃኒቶችን (anticoagulants) መጠቀም እንዲሁም የጠበበውን የሚትራል በር የሚነፋ ቧንቧ መሰል መሳሪያ ወይም ካቴተር በሚትራል በር ውስጥ በማስገባት የጠበበውን የሚትራል በር ማስፋት / (balloon valvotomy) እና የመሳሰሉት ዋንኞች በሚትራል በር መጥበብ ምክንያት ለታመሙ ሰዎች ሊሰጡ የሚችሉ የህክምና መንገዶች ናቸው።
ከላይ በተጠቀሱት የህክምና መንገዶች የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦችን መቆጣጠር በማይቻልበት ወይም ሆኔታው መሻሻል የማያሳይ ከሆነ ወይም የሚትራል በር በከፍተኛ ደረጃ በሚጠብበት ወቅት በቀዶ ጥገና የሚትራል በርን ማስተካከል ወይም በሰው ሰራሽ በር መቀየር አስፈላጊ ይሆናል።