14.2. የቆዳ ቀለም ለውጥ የሚያስከትሉ በልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች ( cyanotic congenital heart diseases)
የቆዳ ቀለም ለውጥ የሚያስከትሉ በልብ እና በደም ቧንቧ አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን በፍጥነት በመለየት አስፈላጊውን ህክምና ማግኘት በማይቻልበት ወቅት ሞትን ጨምሮ የከፋ የጤና ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ። እነዚህ የጤና ችግሮች በህይወት ላይ አደገኛ ጉዳት ወይም በፍጥነት ሞትን ሊያስከትሉ የሚችሉ የጤና ችግሮች ሰለሆኑ ፅንሱ በማሕጸን ውስጥ እያለ ወይም ህጻኑ እንደተወለደ አሰፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።
የቆዳ ቀለም ለውጥ ከሚያስከትሉ በልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች መከሰት ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የቆዳ ቀለም ወደ ሰማያዊ መቀየር ወይም የቆዳ መገርጣት ፣ ጡት መጥባትን ወይም ምግብ መመገብ አለመቻል ወይም ለመመገብ ወይም ለመጥባት በሚሞክሩበት ወቅት የትንፋሽ ማጠር እና የቆዳ ቀለም መቀየር ፣ የዕድገት መቀጨጭ ፣ በእንቅስቃሴ ወቅት የሚፈጠር የትንፋሽ ማጠር ፣ የልብ ምት ፍጥነት መጨመር እና አጠቃላይ የድካም ስሜት መሰማት ፣ በደም ውስጥ የሚገኘው የኦክስጂን መጠን መቀነስ ፣ የልብ ድካም በሽታ ፣ የእጅ ጥፍር መወፈር (clubbing) እና የሰውነት እብጠት ዋንኞቹ ናቸው።
በአጠቃላይ የቆዳ ቀለም ለውጥ የሚያስከትሉ በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት ከሚፈጠሩ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶችን እና ለውጦችን ለመቆጣጠር ወይም በሽታውን ለማከም የተለያዩ የህክምና መንገዶችን መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል። በጥቅም ላይ ከሚወሉ የህክምና መንገዶች መካከል የደክተስ አርተሪኦሰስ ማሻገሪያ እንደተከፈተ እንዲቆይ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን ( የፕሮስታግላንዲን ሆርሞንን በመድኃኒት መልክ መጠቀም) ፣ ከልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ የሚከሰተውን የፈሳሽ መጠን መጨመር ወይም የሰውነት ዕብጠት ለመቀነስ ፈሳሽን ከሰውነት ለማስወገድ የሚረዱ መድኃኒቶችን፣ የልብ ጡንቻ የመኮማተር አቅምን የሚጨምሩ መድኃኒቶችን መጠቀም እንዲሁም በሳንባ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚፈጠር ኢንፌክሽን መከሰትን ለመከላክል የሚረዱ ጸረ ባክትሪያ መድኃኒቶችን መጠቀም እና የቀዶ ጥገና ህክምና ዋንኞቹ ናቸው።
የቆዳ ቀለም ለውጥ ከሚያሰከትሉ በልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት ከሚፈጠሩ የጤና ችግሮች መካከል የትረንከስ አርተሪኦሰስ ቧንቧ ለሁለት አለመከፈል (Persistent Truncus Arteriosus /PTA) ፣ የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ እና የየፑልሞናሪ አርተሪ ከተቃራኒ የልብ ክፍሎች ላይ መነሳት (Transposition of the great Vessels / TPGV) ፣ የትራይካስፒድ በር በትክክል አለመፍጠር (Tricuspid Atresia / TA) ፣ በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት ውስጥ በአንድ ላይ የሚከሰቱ አራት የጤና ችግሮች (Tetralogy of Fallot / ToF) እንዲሁም የፑልሞናሪ ቬን ደምን ከሳንባ በመቀበል ወደ ቀኝ አትሪየም ውስጥ መመለስ (Total anomalous pulmonary venous return / TAPVR) ዋንኞቹ ናቸው።