14.2.1.የትረንከስ አርተሪኦሰስ ቧንቧ ለሁለት አለመከፈል (Persistent Truncus Arteriosus / PTA)
የትረንከስ አርተሪኦሰስ ለሁለት አለመከፍል የጤና ችግር የሚፈጠረው በነርቭ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩት የኒዩራል ክረስት ሴሎች ልብ ወደሚፈጠርበት የፅንሱ ክፍል በመጓዝ የልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት አፍጣጠር ሂደትን ማቀላጠፍ በማይችሉበት ወቅት ነው። የትረንከስ አርተሪኦሰስ ቧንቧን ለሁለት በመክፈል የፑልሞናሪ አርተሪ እና የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ እንዲፈጠሩ የሚያደርገው የአኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም (aorticopulmonary septum) በዋነኝነት የሚሰራው ከኒዩራል ሴሎች ነው።
በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ውስጥ የሚፈጠረው የትረንከስ አርተሪኦሰስ ቧንቧ በአኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም (aorticopulmonary septum) ለሁለት በመከፈል ሁለት ትልልቅ የደም ቧንቧዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። የትረንከስ አርተሪኦሰስ በአኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም ለሁለት መከፈል የተነሳ የሚፈጠሩት ሁለት ትልልቅ የደም ቧንቧዎች የፑልሞናሪ አርተሪ እና የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ናቸው። አኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም ከኒዩራል ሴሎች ልብወደሚሰራበት የፅንሱ የልብ ክፍል መጓዝ ወይም መድረስ አለመቻል የተነሳ በሚገባው መልኩ ያልተሰራ በሚሆንበት ወይም በሚገባው ደረጃ መጠማዘዝ በማይችልበት ወቅት ትረንከስ አርተሪኦሰስን ለሁለት በመከፈል ሁለቱን ትልልቅ የደም ቧንቧዎች መፍጠር አይቻልም። በዚህም ምክንያት ከቀኝ ቬንትሪክል የሚረጨው ያልተጣረቐ ደም እና ከግራ ቬንትሪክል የሚረጨው የተጣራ ደም በአንድ ቧንቧ ወይም በትረንከስ አርተሪኦሰስ ውስጥ በመደባለቅ ወደ ተለያዩ ሰውነት ክፍሎች የሚረጭ ይሆናል።
የትረንከስ አርተሪኦሰስ ለሁለት አለመከፈል የጤና ችግር ጋር በተያያዥነት ሊከሰቱ ከሚችሉ ሌሎች የጤና ችግሮች መካከል የቬንትሪክል ሴፕተም መሽንቆር (VSD) ፣ በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ መታጠፊያ ውስጥ የሚፈጠር የደም ዝውውር መስተጓጉል እንዲሁም በኮሮናሪ አርተሪዎች ላይ የሚፈጠር ጉዳት ዋንኞቹ ናቸው። ይህ ዓይነት የጤና ችግር በዘረ መል ወይም በከሮሞዞሞች ላይ በሚፈጠር ለውጥ የተነሳ ሊከሰቱ ከሚችሉ የጤና ችግሮች ወይም ከዳይጂኦርጅ ሴንድሮም ( Digeorge syndrome) ጋር በተገናኘ ሊከሰት ይችላል።
ከቀኝ የቬንትሪክል የሚረጨው ያልተጣራ ደም እና ከግራ ቬንትሪክል የሚረጨው የተጣራ ደም በአንድ ላይ በመደባለቅ ወደ ተለያዩ የሰወነት ክፍሎች በሚረጭበት ወቅት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በሚደርሰው ደም ውስጥ የሚኖረው የኦክስጂን መጠን በጣም ዝቅተኛ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ህጻናቱ እንደተወለዱ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የቆዳ የቀለም ለውጥ እና ሌሎች እንደ የትንፋሽ ማጠር ፣ የዕድገት መቀጨጭ እንዲሁም በአካላዊ ምርመራ የሚሰሙ ጤነኛ ያለሆነ የልብ ድምጽ መሰማት ዋንኞቹ ናቸው።

ይህ የጤና ችግር በፍጥነት መታከም ይኖርበታል። የበሽተኛውን የጤንነት ሆኔታ ለማስተካከል እና ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶችን እና ለውጦችን ለመቆጣጠር የተለያዩ መድኃኒቶችን ከመጠቀም በተጨማሪ የልብ የቀዶ ጥገና ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።