144.2.2. የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ እና የየፑልሞናሪ አርተሪ ከተቃራኒ የልብ ክፍሎች ላይ መነሳት (Transposition of the great Vessels /TPGV)
በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት ከላይ እንደተገለጸው ከትርንከስ አርተሪኦሰስ በአኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም ለሁለት መከፈል የተነሳ የሚፈጠሩት ሁለቱ ትልልቅ የደም ቧንቧዎች የተለያየ ተግባር ይኖራቸዋል።
የፑልሞናሪ አርተሪ ያልተጣራ ደምን ከቀኝ አትሪየም በመቀበል ወደ ሳንባ እንዲደርስ የሚያደርግ ሲሆን የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ደግሞ የተጣራ ደምን ከግራ ቬንትሪክል በመቀበል ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እንዲደርስ ያደርጋል። ለፑልሞናሪ አርተሪ እና ለትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በትክክል መፈጠር የአኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም በተገቢው ክፍል ላይ ከመገኘት በተጨማሪ የኣኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም በሚገባው መልኩ መጠማዘዝም እጅግ አስፈላጊ ነው። የአኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም በሚገበው መልኩ መጠማዘዝ ሳይችል በሚቀርበት ወቅት የፑልሞናሪ አርተሪ እና የትልቁ ደም ቅዳ መነሻ ክፍል ከተቃራኒ የልብ ክፍሎች ላይ እንዲሆን ያደርጋል።
ስለዚህም የኣኦርቲኮፑልሞናሪ ሴፕተም በተገቢው መልኩ መጠማዘዝ ሳይችል ሲቀር የፑልሞናሪ አርተሪ ከግራ ቬንትሪክል በመነሳት የተጣራውን ደም መልሶ ወደ ሳንባ የሚወስድ ሲሆን ትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ደግሞ ከቀኝ አትሪየም ላይ በመነሳት ያልተጣራውን ደም በመቀበል ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እንዲደርስ ያደርጋል። ስለዚህም በደም ውስጥ የሚኖረው የኦክስጂን መጠን እጅግ ዝቅተኛ ስለሚሆን በዚህ የጤና ችግር የተጠቁ ህጻናት በሚውለዱበት ወቅት የቆዳ ቀለም ለውጥ እና ሌሎች ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ።

የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ እና የፑልሞናሪ አርተሪ ከተቃራኒ የልብ ክፍሎች ላይ መነሳት የጤና ችግር ጋር በአንድ ላይ ከሚፈጠሩ ሌሎች የጤና ችግሮች መካከል የቬንትሪክል ሴፕተም መሸንቆር ፣ ከግራ ቬንትሪክል የሚረጨው የደም ፍሰት መዘጋት ፣ በትክክል የማይሰሩ የልብ በሮች እና በኮሮናሪ አርተሪ ላይ የሚፈጠር ጉዳት ዋንኞቹ ናቸው።
የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ እና የፑልሞናሪ አርተሪ ከተቃራኒ የልብ ክፍሎች ላይ መነሳት የጤና ችግር መንስሄ በትክክል የሚታወቅ ባይሆንም በስኳር በሽታ ከተጠቁ እናቶች መወለድ እንዲሁም በዘረ መል ወይም ከሮሞዞም ላይ የሚፈጠር ለውጥ (ዳይጂኦርጅ ሲንድሮም / DiGeorge syndrome) ለዚህ የጤና ችግር መከሰት ተጋላጭነት እንዲጨምር ሊያደርጉ የሚችሉ ሆኔታዎች ናቸው።
ከዚህ የጤና ችግር ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የቆዳ ቀለም ለውጥ ፣ የልብ ምት ፍጥነት መጨመር ፣ በአካላዊ ምርመራ የሚስማ ጤነኛ ያለሆነ የልብ ድምጽ መሰማት ዋንኞቹ ናቸው።
ይህን የጤና ችግር ፅንሱ በማሕጸን ውስጥ እያለ በአልትራሳውንድ ምርመራ መለየት የሚቻል ሲሆን የኢኮካርዲዩግራም ምርመራ ፣ የኤም አር አይ ፣ የደረት ራጅ እና የኤሌክትሮካርዲዩግራም ምርመራ በማድረግ የተከሰተውን የጤና ችግር ደረጃ መለየት ይቻላል።
ከበሽታው ጋር የሚከሰቱ ምልክቶችን እና ለውጦችን ለመቆጣጠር የፕሮስታግላንዲን ሆርሞንን በመድኃኒት መልክ በመጠቀም የደክተስ አርተሪ ኦሰም ማሻገሪያ እንደተከፈተ እንዲቆይ ማድረግ አሰፈላጊ ሲሆን በዚህ የጤና ችግት የተጠቁ ህጻናት አስቸኳይ የሆነ የልብ የቀዶ ጥገና ህክምና ካልተደረገላቸው በስተቀር በህይወት የመቆየት እድላቸው እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል።