Course Content
ምዕራፍ አሥራ አራት : በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች
0/16
ምዕራፍ አሥራ አምሥት : ከልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮች (Cardiac electrical system abnormalities)
0/16
ምዕራፍ አስራ ሰባት : በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Valvular heart diseases)
0/16
ምዕራፍ ሃያ አንድ : የልብ ድካምበሽታ (Heart failure )
0/1
ምዕራፍ ሃያ ሦስት : በደም ቧንቧዎች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Vascular diseases)
0/22
በልብ እና በደም ቧንቧ ሥር ዓት ክፍሎች ውስጥ ሊፈጠሪ የሚችሉ የጤና ችግሮች (Pathology of Cardiovascular System)

14.2.4. በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት ውስጥ በአንድ ላይ የሚከሰቱ አራት የልብ ጤና ችግሮች  (Tetralogy of Fallot / ToF)

  ይህ የጤና ችግር በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት ከሚፈጠር እክል የተነሳ የሚከሰት የጤና ችግር ነው። በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት ውስጥ በአንድ ላይ የሚከሰቱ አራት የጤና ችግሮች  በዋናነት የሚከሰተው በቬንትሪክሎች መካከል የሚገኘው የላይኛው የቬንትሪክል ሴፕተም እንዲሁም በሌሎች የልብ ክፍሎች አፈጣጠር ሂደት ወቅት ከሚፈጠሩ እክሎች ወይም ጉድለቶች የተነሳ ነው። ይህ የጤና ችግር ስሙ እንደሚያመለክተው ከአራት ዋና የልብ ችግሮች ጋር በተያያዘ የሚከሰት የልብ የጤና ችግር ነው።

   እነዚህም አራት የልብ የጤና ችግሮች የፑልሞናሪ አርተሪ በር መጥበብ ( pulmonary valve stenosis) ፣ የቀኝ ቬንትሪክል ግድግዳ መወፈር (ventricular hypertrophy) ፣ የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በግራ እና በቀኝ ቬንትሪክሎች መካከል ላይ መገኘት (overriding aorta) እና በቀኝ እና በግራ ቬንትሪክሎች መካከል የሚገኘው ግድግዳ ወይም የቬንተሪክል ሴፕተም መሽንቆር (VSD) ናቸው። 

    የቀኝ ቬንትሪክል በጠበበው የፑልሞናሪ አርተሪ በር በኩል ደምን ለመርጨት በሚያደርገው ከፍተኛ ሥራ ምክንያት የቀኝ ቬንትሪክል ግድግዳ በጣም ይወፍራል። ይህም በቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ የሚፈጠረው ግፊት እንዲጨምር ስለሚያድርግ ያልተጣራ ደም ከቀኝ ቬንትሪክል ወደ ግራ ቬንትሪክል በማለፍ በግራ ቬንትሪክል ውስጥ ከሚገኝው ከተጣራው ደም ጋር ይደባለቃል። 

    ይህም የተደባለቀ ደም በትልቁ ደም ቧንቧ በኩል ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ይረጫል። በተደባለቀው ደም ውስጥ የሚገኘው የኦክስጂን መጠን በጣም ዝቅተኛ ሰለሚሆን ህጻናቱ በሚወለዱበት ወቅት የቆዳ ለውጥ እና ሌሎች ምልክቶችን የሚያሳዩ ይሆናል። እነዚህ ህጻናት በሚያልቅሱበት ፣ ትኩሳት በሚይዛቸው ጊዜ እና እንቃስቃሴ በሚያደርጉበት ውቅት ከበሽታው ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦች ይባባሳሉ ። ምክንያቱም ከላይ የተገለጹትን ሆኔታዎች ለመቋቋም ይቻል ዘንድ የቀኝ  ቬንትሪክል በጠበበው የፑልሞናሪ አርተሪ በር በኩል ደምን ለመርጨት በሚያደርገው ጥረት በቀኝ ቬነንትሪክል ውሰጥ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያደረጋል። በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው ያልተጣራ ደም ከቀኝ ቬንትሪክል በመውጣት ወደ ግራ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገባ ይሆናል ። ወደቬንትሪክል ውሰጥ የሚገባው ደም በሚረጨበት ወቅት በደም ውስጥ የሚኖረው የኦክስጂን መጠን ሰለሚቀንስ የቆዳ ቀለም መለወጥ እንዲሁም ሌሎችም ምልክቶቸ እና ለውጦቸ በተባባሰ ሆኔታ የሚከሰቱ ይሆናል። 

    በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት ውስጥ በአንድ ላይ የሚከሰቱ አራት የልብ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች ዓይነት እና ደረጃ በፑልሞናሪ አርተሪ በር ላይ በሚከሰተው የጥበት መጠን እንዲሁም በቀኝ እና በግራ የልብ ክፍሎች ውስጥ መካከል በሚኖረው የደም መደባለቅ ሆኔታ ላይ የሚመሰረት ይሆናል። የፑልሞናሪ በር መጥበብ በከፍተኛ ደረጃ ላይ በሚገኝበት ወቅት የቀኝ ቬንትሪክል በጠበበው የአርተሪ በር በኩል ደምን ለመርጨት በሚያደርገው ከፍተኛ ጫና እና ሥራ የተነሳ የቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ የሚፈጠረው የግፊት መጠን እንዲጨምር እንዲሁም የቀኝ ቬንትሪክል ግድግዳ እንዲወፍር ያደርጋል። 

     በቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ ከሚፈጠረው ከፍተኛ የግፊት መጠን የተነሳም ከፍተኛ መጠን ያለው ያልተጣራ ደም ከቀኝ ቬንትሪክል ወደ ግራ ቬንትሪክል ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ዝቅተኛ የኦክስጂን መጠን ያለው ደም በግራ ቬንትሪክል በኩል ከሰውነት የሚረጭ ይሆናል። 

       በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት  ውስጥ በአንድ ላይ ከሚከሰቱ አራት የልብ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካክል የቆዳ ቀለም ለውጥ ፣ ህጻኑ ጡት በሚጠጣበት ፣ በሚያለቅስበት ፣ ዓይነ ምድር በሚያስወግድበት ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በሚያደርግበት ወቅት የቆዳ ቀለም ለውጥ ወይም የቆዳ መግርጣት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። 

    በዚህ የጤና ችግር የተጠቁ ህጻናት በእግራቸው ላይ ቁጢጥ ብለው (squat)  በሚቀመጡበት ወቅት ወደልብ የሚመለሰው የደም መጠን እንዲጨምር በማድረግ ከቀኝ  ቬንትሪክል የሚረጨው ከፍተኛ መጠን ያለው ደም በፑልሞናሪ አርተሪ በር በኩል አልፎ ወደ ሳንባ የሚረጭ ይሆናል። ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው ደም በሳንባ ተጣርቶ በግራ ቬንትሪክል በኩል ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ስለሚረጭ  የሚፈጠሩ ምልክቶች እና ስሜቶች  የሚቀንሱ ይሆናል። 

   ምስል  በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት ውስጥ በአንድ ላይ የሚከሰቱ አራት የልብ የጤና ችግሮች 

     ይህን የጤና ችግር ፅንሱ  በማህጸን ውስጥ እያለ በኢኮካርዲዩግራም ምርመራ መለየት ወይም ማወቅ የሚቻል ሲሆን ህጻኑ ከተወለደም በኋላ የአኮካርዲዩግራም ምርመራ ፣ የደረት ራጅ ምርመራ ወይም  የኤለክትሮካርዲዩግራም ምርመራ በመጠቀም የተፈጠረውን የጤና ችግር ዓነት እና ከተፈጠረው የጤና ችግር ጋር በተገናኘ የተፈጠሩ ለውጦችን መለየት ይቻላል። 

   በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት  ውስጥ በአንድ ላይ ከሚከሰቱ አራት የልብ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ  የሚፈጠሩ ምልክቶችን እና ለውጦችን ለመቆጣጠር በቂ መጠን ያለው ኦክስጂን ፣ እግርን ከደረት ጋር አጣብቆ መቀመጥ (squatting) ፣ ህጻኑ እንዲርጋጋ የሚያድርጉ መድኃኒቶችን መጠቀም ፣ በደም ሥር በኩል የሚሰጥ  ፈሳሽ  እንዲሁም የልብን የመኮማተር አቅም የሚቀንሱ መድሃኒቶችን መጠቀም አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ።  በተጨማሪም የልብ ድካም ምልክቶች እና ለውጦች በሚፈጠሩበት ወቅት የልብ ጡንቻ መኮማተር እንዲጨምር የሚያደርጉ የዲጆክሲን መድኃኒቶችን መጠቀም አስፈልጊ ሊሆን ይችላል። 

የተከሰተውን የጤና ችግር በሚገባ ለማከም ህጻኑ በተወለደ የመጀመሪያው ዓመት ውስጥ በልብ ቀዶ ጥገና ህክምና  የተፈጠረውን ችግር ማስተካከል አስፈላጊ ይሆናል ።