16. ከልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮች (Cardiac electrical system abnormalities)
የልብ ምት ሥርዓት በተገቢው መልኩ እንዲከናወን የልብን ምት ፍጥነት የሚቆጣጠረው የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ በተገቢው መልኩ መፈጠር እና መንቀሳቀስ ወይም በትክክል መስራት መቻል አለበት። የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ የሚፈጠረው እና የሚመራው በሳይኖአትሪያል ወይም በሳይነስ ኖድ (sinus node) አማካኝነት ነው።
ልብ በራሱ ከሚነሳ እና ቀደም ተከተሎን ጠብቆ በልብ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በሚጓዝ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ የልብ ክፍሎች በአንድ ጊዜ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን እንዲችሉ የሚያደርግ ዋና የልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት ክፍል ነው። በቀኝ አትሪየም ውስጥ የሚገኘው እና የልብ የኤሌክትሪክ አንቅስቅሴ መነሻ ወይም ልብ የልብ ምትን በራሱ እንዲያነሳሳ የሚያደርገው ወይም የልብን የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ የሚመራው የልብ ክፍል ሳይኖአትሪያል ወይም ሳይነስ ኖድ (sinus node) ተብሎ ይጠራል። የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ከሳይነስ ኖድ በመነሳት የግራ እና የቀኝ አትሪየምን በሙሉ ካዳረሰ በኋላ በአትሪዩቬንትሪኪዩላር ኖድ በኩል በማለፍ ወደ የግራ እና የየቀኝ የቬንትሪክል ክፍሎች ውስጥ የሚደረስ ይሆናል።
በሳይነስ ኖድ ውስጥ የሚፈጠረው የልብ የኤሌክትሪከ እንቅስቃሴ ከሳይነስ ኖድ በመነሳት ወደ ግራ አትሪየም ክፍል ውስጥ በባችማንስ የኤሌክትሪክ መንገዶች (Bachmann’s bundle) በኩል የሚዳረስ ሲሆን ከሳይነስ ኖድ በቀኝ አትሪየም ውስጥ አልፎ በኖዶች መካከል ማለትም በሳይነስ ኖድ እና በአትሪኦቬንትሪኪዩላር ኖድ መካከል በሚገኘው መንገድ (internodal tracts) በኩል አድርጎ ወደ አትሪዩቬንትሪኪዩላር ኖድ የሚደርስ ይሆናል።
በአትሪኦቨንትሪኪዩላር ኖድ ውስጥ የሚደረሰው የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ወደ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው በቀኝ እና በግራ ቬንትሪክሎች መካከል በሚገኘው በዋናው የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ማሳለፊያ መንገድ ፧Bundle of his) በኩል ይሆናል። ከሳይነስ ኖድ የሚነሳው የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ዋናው የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ማሳላፊያ መንገድን አልፎ በቀኝ እና በግራ የልብ የኤሌክትሪክ ማሳለፊያዎች በኩል ወደ ፑርኪንጂ ደሮች ውስጥ በመግባት በቀኝ እና በግራ ቬንትርክሎች ውስጥ ለሚገኙ የልብ ሴሎች የሚደርስ ይሆናል።

ምስል 15 ፡1 የልብ የኤሌክትሪክ አንቅስቃሴ
የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ፍስት በአትሪየም ውስጥ በሚያልፍበት ወቅት አትሪየም እንዲኮማተር ያደርጋል። አትሪየም በሚኮማተርበት ተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ቬንትሪክል በመለጠጥ ደምን ከአትሪየም ይቀበላል። ይህ የአትሪየም መኮማተር እና የቬንትሪክል በመለጠጥ ደም የመቀበያ ግዜ ቬንትሪክል የሚለጠጥበት ክፍለ ግዜ ወይም የዳያስቶሊክ ክፍለ ግዜ (diastolic phase) ተብሎ ይጠራል።
የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ በአትሪየም ውስጥ ካለፈ በኋላ በአትሪየም እና በቬንትሪክል መካከል በሚገኘው በአትሪኦቬንትሪኪዪላር ኖድ ውስጥ ከማለፉ በፊት የኤሌክትሪክ ፍሰቱ ለተወሰኑ ሰኮንዶች የሚዘገይ ይሆናል። ይህም መዘግየት ለአትሪየም መኮማተር እና ለቬንትሪክል መለጠጥ መጠናቀቅ በቂ ግዜ ይሰጣል። የልብ የኤሌክትሪክ ፍሰት ከአትሪዩቬንትሪኪዩላር ኖድ በመውጣት ወደ ቬንትርክል ሴሎች በሚደርስበት ወቅት የቬንትሪክል መኮማተር እንዲፈጠር ያደርጋል። ቬንትሪክል በሚኮማተርበት ተመሳሳይ ግዜ ውስጥ አትሪየም በመለጠጥ ደም ይቀበላል። ይህ የቬንትሪክል መኮማተር ፣ የአትሪም መለጠጥ እና ደም መቀቢያ ጊዜ ቬንትሪክል የሚኮማተርበት ክፍለ ግዜ ወይም የሲስቶሊክ ክፍለ ግዜ (systolic phase) ተብሎ ይጠራል።
ከላይ በተገለጸው መሰረት በልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ የተነሳ የሚፈጠረው የአትሪየም መኮማተር ፣ የአትሪየም መለጠጥ ፣ የቬንትሪክል መኮማተር ፣ የቬንትሪክል መለጠጥ እና ሌሎችምም የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴን ተከትሎ የሚፈጠሩ ሂደቶች ከልብ ምት ሆኔታ ጋር በተዛመደ መልኩ በኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ በሥህላዊ መልክ ሞገዶችን ፣ ርቀቶችን እና ሴግመንቶችን በመጠቀም ሊገለጹ ይችላሉ።
- የፒ / P ሞገድ (P wave) – የአትሪየም መኮማተር
- የፒ አር / PR ርቀት (PR interval) – የልብ የኤሌክትሪክ ፍሰት ከአትሪየም ተነስቶ ቬንትርክል እስከሚደርስ ደረስ የሚወስደው ጊዜ ·
- የኪው አር ኤስ / QRS ኮምፕሌክስ (QRS complex) – የቬንትሪክል መኮማተር
- የኪው ቲ / QTሴግመንት (QT segment ) – ቬንትርክል ለመኮማተር እና ለመለጠጥ የሚወስደው ጊዜ
- የ ቲ / T ሞገድ (T wave) – የቬንትሪክል መለጠጥ
- የኤስ ቲ / ST ሲግመንት (ST segment) – በቬንትሪክል መኮማተር እና መለጠጥ መካከል የሚወስደው ጊዜ
ምስል 15 ፡ 2 ከልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች
በልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ የተለያዩ እክሎች የልብ ምት መዛባት የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ጤነኛ ወይም ትክክለኛ የልብ ምት የሚባለው ያልተዘበራረቀ እና ፍጥነቱም በደቂቃ ከ 60 -100 ሆኖ ሲገኝ ነው። የልብ ምት ፍጥነት በደቂቃ ከ 100 በላይ ሆኖ ሲገኝ ፈጣን የልብ ምት (tachycardia) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የልብ ምት ፍጥነት በደቂቃ ከ 60 በታች ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የዘገየ የልብ ምት ፍጥነት (bradycardia) ተብሎ ይጠራል። የልብ ምት ፍጥነት ከሚጠበቀው መጠን በታች ወይም በላይ መሆን ወይም የልብ የኤሌክትሪክ እንቅሰቃሴ አፈጣጠር ወይም ፍሰት ከጤነኛ አካሂድ ወይም መስመር ውጭ ከመሆኑ የተነሳ የተዘበራረቀ የልብ ምት የሚፈጠርበት ሆኔታ ደግሞ የተዛባ የልብ ምት (arrhythmia) ተብሎ ይጠራል።