17.1.2.1. የትራይካስፒድ በር መጥበብ (Tricuspid stenosis)
የትራይካስፒድ በር መጥበብ ወይም የትራይካስፒድ በር በሚፈለገው መጠን መከፈት አለመቻል የልብ የጤና ችግር አልፎ አልፎ የሚከሰት የጤና ችግር ሲሆን በሚከሰትበትም ወቅት አብዛኛውን ግዜ የሚከስተው የሚትራል በር መጥበብ የልብ የጤና ችግር ባላባቸው በሽተኞች ላይ ነው። የትራይካስፒድ በር መጥበብ ዋና መንስሄ በተደጋጋሚ ከሚከሰት ከስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በሰውነት የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች የተነሳ በልብ በሮች ላይ ከሚከሰት የጤና ችግር ጋር በተገናኘ ነው።
የትራይካስፒድ በር መጥበብ በሚፈጠርበት ወቅት ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ተሰብስቦ ወደ ቀኝ አትሪየም ውስጥ የሚገባው ደም በትራይካስፒድ በር በኩል አልፎ ወደ ቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ ሙሉ በሙሉ መግባት አይችልም። በዚህም በቀኝ አትሪየም ውስጥ የሚኖረው የደም እና የግፊት መጠን የሚጨምር ይሆናል። በአትሪየም ውስጥ የሚገኘው የደም እና የግፊት መጠን በሚጨምርበት ወቅት ደምን ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በሚያመጡት የላይኛው እና የታችኛው ትልቁ የደም መልስ ቧንቧዎች ውስጥ የሚገኘው የግፊት መጠንም የሚጨምር ይሆናል። ይህም ሆኔታ ከሰውነት ክፍሎች ተስብስቦ የሚመጣው ደም ወደ ልብ ውስጥ እንዳይገባ ስለሚገድብ በአንገት አካባቢ በሚገኙ የደም መልስ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚከማቸው የደም መጠን እንዲጨምር እና በአንገት አካባቢ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች ተገታትረው እንዲታዩ ያደርጋል።
በተጨማሪም ከሰውነት ተስብስቦ የሚመጣው የሰውነት ፈሳሽ ወደ ልብ ውስጥ መግባት ስለማይችል በጉበት ፣ በሆድ እና በታችኛው የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በመጠራቀም በእግር እና በሆድ ውስጥ የሰውነት ዕብጠት የሚከሰት ይሆናል። ወደ ልብ የሚገባው የደም መጠን ስለሚቀንስም በየደቂቃው ከልብ የሚረጨው የደም መጠን ይቀንሳል።
የትራይካስፒድ በር መጥበብ በሚከሰትበት ወቅት የትንፋሽ ማጠር ፣ የልብ መጠን መጨመር ፣ በእግር ላይ የሚከሰት እብጠት መታየት እና በሆድ ውስጥ የፈሳሽ መጠራቀም እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። የትራይካስፒድ በር መጥበብ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ደግሞ በቀኝ የልብ ክፍል ውስጥ የሚከሰት የልብ ድካም በሽታ፣ በጉበት ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት የተነሳ የአይን ቤጫ መሆን ፣ የቆሽት መጠን መጨመር እና በአንገት አካባቢ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች መገታተር እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል። በተጨማሪም ቬንትሪክል በሚለጠጥበት ወይም የቀኝ አትሪየም በሚኮማተርበት ወቅት በትራይካስፒድ በር ላይ የሚሰማ ጤነኛ ያለሆነ የልብ ምት ድምጽ (diastolic murmur) የሚሰማ ይሆናል።
የትራይካስፒድ በር መጥበብ የልብ የጤና ችግር መከሰቱን ለማወቅ ከሚደረጉ ምርመራዎች መካከል የኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርምራ የቀኝ አትሪየም ግድግዳ መወፈርን (tall P wave) ሊያሳይ ይችላል። የደረት የራጅ ምርመራ ደግሞ የግራ አትሪየም መጠን መጨመርን ሊያሳይ ይችላል። በኢኮካርዲዩግራም ምርመራ የትራይካስፒድ በር መወፈርን ፣ በአትሪየም እና በቬንትሪክ መካከል የግፊት መጠን ለውጥን እና የትራይካስፒድ በር መጠንን ማወቅ ይቻላል።
በደም መልስ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚፈጠረውን የደም እና የግፊት መጠን መጨመር በምግብ እና መጠጥ መልክ የሚወሰደውን የጨው መጠን እና የፈሳሽ መጠን በመቀነስ ፣ እረፍት በማድረግ ወይም እንቅስቃሴን በመቀነስ ፣ ፈሳሽ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን በመጠቀም እና በመሳስለት ህክምናዎች በሽተኛውን ለቀዶ ጥገና ህክምና ማዘጋጀት አስፈላጊ ይሆናል። ለትራይካስፒድ በር መጥበብ የልብ የጤና ችግር ዋና ህክምና በቀዶ ጥገና የተጎዳወን የትራይካስፒድ በር መጠገን (valve repair) ወይም መጠገን በማይቻልበት ወቅት ደግሞ በሌላ የትራይካስፒድ በር መቀየር (valve replacement) ነው። አንድ አንድ ግዜ የትራይካስፒድ በር መጥበብን ለማስፋት በትለልቅ የደም ቧንቧዎች በኩል በሚገባ ቀጭን ቧንቧ መስል መሳሪያ ወይም ካቴተር ወደ ትራይካስፒድ በር ውስጥ በማስገባት እና እንደ ፊኛ በመነፋት የጠበበውን የትራይካስፒድ በር ለማስፋት (balloon valvuloplasty) የሚረዳ ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።