17.1.2.2 የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል (Tricuspid regurgitation)
የትራይካስፒድ በር በትክክል መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር ዋና መንስሄ በተለያዩ ምክንያቶቸእ የቀኝ ቬንትሪክል ከሚገባው መጠን በላይ መለጠጥ ነው። የቀኝ ቬንትሪክል ከመጠን በላይ እንዲለጠጥ ከሚያደርጉ ሆኔታዎች መካከል የፑልሞናሪ አርትሪ የግፊት መጠን መጨመር ( pulmonary hypertension)፣ ወደ ልብ ከሚደርሰው የደም ወይም የኦክሰጂን መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የከፋ የልብ የጤና ችግር (myocardial infarction) ዋንኞቹ ናቸው። በተጨማሪም በልብ አፈጣጠር ወቅት የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮች ፣ ከስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በሰውነት የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲኖች የተነሳ በልብ በሮች ላይ የሚፈጠር የጤና ችግር ፣ በልብ ውስጥ የሚፈጠር ኢንፌክሽን (endocarditis) ፣ ለጨረር መጋለጥ እንዲሁም በልብ አፈጣጠር ሂደት ወቅት የትራይካስፒድ በር በቬንትሪክል ውስጥ መገኘት (Ebstein’s malformation) በረጅም ግዜ የሚከሰት የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል እንዲከሰት ሊያደርጉ የሚችሉ ሆኔታዎች ናቸው።
የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር መከሰትን ተከትሎ የቀኝ ቬንትሪክል በሚኮማተርበት ወቅት ደም ተመልሶ ወደ ቀኝ አትሪየም ውስጥ የሚገባ ይሆናል። የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦች በፑልሞናሪ አርተሪ ውስጥ በሚኖረው የግፊት መጠን ላይ የሚወሰኑ ይሆናል። የፑልሞናሪ አርተሪ የደም ግፊት መጠን በሚጨምርበት ወቅት ከቀኝ ቬንትሪክል ወደ ቀኝ አትሪየም ተመልሶ የሚገባው የደም መጠን የበለጠ የሚጨምር ይሆናል።
የትራይካስፒድ በር በትክክል መዘጋት አለመቻል ለረጅም ግዜ በሚቆይበት ወቅት የቀኝ ቬንትሪክል ከመጠን በላይ እንዲለጠጥ ፣ የፑልሞናሪ አርተሪ የደም ግፊት መጠን እንዲጨምር እና በያአንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ከልብ የሚረጨው የደም መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል። ይህም ሆኔታ አካላዊ እንቅስቃሴ በሚሠራበት ወቅት የትንፋሽ ማጠር እንዲፈጠር ያደርጋል።
በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር በሚከሰትበት ወቅት በበሽተኛው ላይ ምንም ዓይነት ምልክት እና ለውጥ ላይታይ ይችላል። ብዙሁን ግዜ የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል እንደ የፑልሞናሪ አርተሪ የደም ግፊት መጠን መጨመር ፣ ከሚትራል በር መጥበብ ወይም በልብ የግራ ክፍል ላይ የሚከሰት የልብ ድካም ያሉ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ ስለሚከሰት በበሽተኞች ላይ የሚታዩት ምልክቶች እና ለውጦች ከእነዚሁ የጤና ችግሮች ጋር የተያያዙ ናቸው። የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር ለብቻው በሚከሰትበት ወቅት ከሚታዩ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የድካም ስሜት መሰማት ፣ የትንፋሽ ማጠር ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ የጡንቻዎች መጠን መቀነስ ፣ የሰውነት ክብደት መጠን መጨመር እና በሰውነት ላይ የሚፈጠር ዕብጠት ጥቂቶቹ ናቸው።
የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር በሚከሰትበት ወቅት በአካላዊ ምርምራ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል በአንገት ላይ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች መገታተር ፣ የጉበት መጠን መጨመር ፣ በሆድ ውስጥ የፈሳሽ መጠን መጨመር ፣ በሆደ የቀኝ የላይኛው ክፍል ላይ በሚጫንበት ወቅት በአንገት አካባቢ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚታየው የደም ቧንቧዎች መገታተር መጨመር (hepatojugular reflux) እንዲሁም አየር ወደ ሳንባ ውስጥ በሚገባበት ወይም አየር ወደ ሳንባ ውስጥ በሚሳብበት ወቅት በሚትራል በር ላይ የሚሰማ ጤነኛ ያልሆነ የልብ ምት ድምጽ መሰማት (holosystolic murmur (Carvallo’s sign) ዋንኞቹ ናቸው።
የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር መከሰቱን ለማወቅ ከሚረዱ የምርመራ መንገዶች መካከል ፡ በኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ ወደ ልብ ከሚደርሰው የደም መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ ከሚፈጠር የከፋ የልብ የጤና ችግር የተነሳ በልብ ጡንቻ ላይ የሚፈጠረውን ጉዳት ወይም የቀኝ አትሪየም ግድግዳ መወፈርን ሊያሳይ ይችላል።
የደረት ራጅ ምርመራ የቀኝ አትሪየም ወይም የቀኝ ቬንትሪክል መጠን መጨመርን ሊያሳይ ይችላል። የኢኮካርዲዮግራም ምርመራ የቀኝ አትሪየም እና የቀኝ ቬንትሪክል ግድግዳ መወፈር ፣ በልብ ግድግዳ ላይ የተፈጠረ እና የዳነ ቁስለት መኖሩን ፣ የትራይካስፒድ በር ሆኔታን እና መጠን እንዲሁም በትራይካስፒድ በር ውስጥ የሚኖረውን የደም ፍሰት አቅጣጫ ሊያሳይ ይችላል።
በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር እና የልብ ድካም በሽታ ምልክቶች የሚታይባቸው ሰዎች ፈሳሽ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን በተለይም የአልዶስቴሮን ሆርሞንን ተግባር የሚገድቡ መድኃኒቶችን መጠቀም በሰውነት ውስጥ የተከማቸውን ፈሳሽ ለመቀነስ እና የበሽተኛውን የጤንነት ሆኔታ ለማሻሻል ይረዳል።
የፑልሞናሪ አርተሪ የደም ግፊት መጠን መጨመርን ወይም በፑልሞናሪ አርተሪ ውስጥ የሚፈጠረውን ግድብት ለመቀነስ የሚረዱ መድኃኒቶችን መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ከላይ በተጠቀሱት የህክምና መንገዶች በቂ የጤንነት መሻሻል ካልተገኘ ወይም በከፋ ደረጃ ላይ የሚገኝ የትራይካስፒድ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች የትራይካስፒድ በርን ለመጠገን ወይም ለመቀየር የልብ የየቀዶ ጥገና ህክምና ሊያስፈልጋቸው ይችላል።