Course Content
ምዕራፍ አሥራ አራት : በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች
0/16
ምዕራፍ አሥራ አምሥት : ከልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮች (Cardiac electrical system abnormalities)
0/16
ምዕራፍ አስራ ሰባት : በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Valvular heart diseases)
0/16
ምዕራፍ ሃያ አንድ : የልብ ድካምበሽታ (Heart failure )
0/1
ምዕራፍ ሃያ ሦስት : በደም ቧንቧዎች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Vascular diseases)
0/22
በልብ እና በደም ቧንቧ ሥር ዓት ክፍሎች ውስጥ ሊፈጠሪ የሚችሉ የጤና ችግሮች (Pathology of Cardiovascular System)

16.1.3.2. የትልቁ ደም ቅዳ መዘጋት አለመቻል (Aortic regurgitation)

    የትልቁ ደም ቅዳ መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር የሚፈጠረው የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር ከግራ ቬንትሪክል ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ የሚረጨው ደም ተመልሶ ወደ ግራ ቬንትሪክል ውስጥ እንዳይገባ መገደብ ወይም ማቆም በማይችልበት እና ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ውስጥ የሚረጨው ደም ተመልሶ ወደ ግራ ቬንትሪክል ውስጥ በሚገባበት ወቅት ነው።

   የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር መንስሄ ከሚሆኑ ሆኔታዎች መካከል የደም ግፊት መጠን መጨመር እና በኮሮናሪ አርተሪ ውስጥ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች የተነሳ በልብ ጡንቻ ላይ የሚፈጠር ጉዳት ዋንኞቹ ናቸው። በተጨማሪም የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ  ግድግዳ እንዲሰፋ የሚያድርጉ የተለያዩ የጤና ችግሮችም  የትልቁ ደም ቅዳ መዘጋት አለመቻል የጤና ችግር እንዲከሰት ሊያደርጉ ይችላሉ። ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ግድግዳ ላይ የተሰራጨ የጭበጥ ኢንፌክሽን ፣ በጀርባ እና በዳሌ አጥንቶች መገጣጠሚያዎች እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ብግነት የሚያስከትል የጤና ችግር (ankylosing spondylitis )፣ በዘር መል ወይም ጂን ላይ ለውጥ የተነሳ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ማለትም በአጥንቶች ፣ በቆዳ ፣ በአይን እና በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ግድግዳ ላይ ጉዳት የሚያስከትል የጤና ችግር ወይም የማርፋን ሲንድሮም (Marfan’s syndrome) ፣ የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ግድግዳ መለጠጥ እና መሰርጎድ ( aortic aneurysm) ፣ የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ግድግዳ መሰንጠቅ ( aortic dissection) እና  በቀጥታ በትልቁ ደም ቅዳ ላይ የሚከሰት ጉዳት ዋንኞቹ በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ላይ ጉዳት በማስከትል የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር እንዲከሰት ሊያደርጉ የሚችሉ ሆኔታዎች ናቸው። ከላይ የተገለፁት ሆኔታዎች የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ግድግዳ እንዲለጠጥ እና የትልቁ ደም ቅዳ በር ተከፋቾች ወይም ካስፒዶች እንዲራራቁ በማድረግ የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር በትክክል መዘጋት እንዳይችል ሊያደርጉ ይችላሉ።

   ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ውስጥ የሚረጨው ደም ተመልሶ ወደ ግራ ቬንትሪክል በሚገባበት ወቅት በግራ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገኘው የደም መጠን የሚጨመር ይሆናል። በግራ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገኘው የደም መጠን በሚጨምርበት ወቅት ደግሞ የግራ ቬንትሪክል ግድግዳ በከፍተኛ ደረጃ ይለጠጣል። ይህም ከሚገባው በላይ የግራ ቬንትሪክል መለጠጥ የቬንትሪክል የመኮማተር አቅም እንዲቀንስ ያደርጋል። በግራ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገኘው የደም መጠን በከፍተኛ መጠን መጨመርን ተከትሎ ቬንትሪክል በሚኮማተርበት ወቅት ደም ከግራ ቬንትሪክል ወደ ግራ አትሪየም እንዲገባ ወይም የሚትራል በር በትክክል መዘጋት እንዳይችል ሊያደርግ ይችላል።

   በያአንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ክልብ የሚረጨው ከፍተኛ መጠን ያለው ደም ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ውስጥ ከተረጨ በኋላ ቬንትሪክል በሚለጠጥበት ወቅት የተወሰነው ደም ተመልሶ  ወደ ቬንትሪክል ውስጥ ስለሚመለስ ቬንትሪክል በሚለጠጥበት ወቅት በደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚኖረው የግፊት መጠን (diastolic pressure) በከፍተኛ መጠን የሚቀንስ ይሆናል። በዚህም የተነሳ በሰውነት የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚፈጠረው ሞገደ ትርታ በሃይል መጥቶ በፍጥነት የሚጠፋ (bounding pulsation) ዓይነት ይሆናል። በተጨማሪም ሞገደ ትርታ በሚመታበት ወቅት የቬንትሪክል መኮማተርን ተከትሎ ጭንቅላት ወደ ፊት እና ወደ ኋላ እንዲንቀሳቀስ (head bob) ሊያደርግ ይችላል።

   የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግርን ተከትሎ ከሚታዩ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የትንፋሽ ማጠር ፣ ቬንትሪክል በሚለጠጥበት ወቅት በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር ላይ የሚሰማ ጤነኛ ያለሆነ የልብ ምት ድምጽ (diastolic murmur) ፣ ዓይነት ሦስት ተጨማሪ የልብ ምት ድምጽ (S3) ፣ በሃይል መጥቶ በፍጥነት የሚጠፋ ሞገደ ትርታ እና የጭንቅላት ወደ ፊት እና ወደ ኋላ መንቀሳቀስ  (head bob፧ ዋንኞቹ ናቸው።

የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር መከሰቱን ለማወቅ ፡ የኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ የግራ ቬንትሪክል የግድግዳ ውፍረት መጨመርን ሊያሳይ ይችላል። በደረት ራጅ ምርመራ የግራ ቬንትሪክል መጠን መጨመርን እና የትልቁ ደም ቅዳ ግድግዳ መስፋትን ሊያሳይ ይችላል። የኢኮካርዲዮግራም ምርመራ የግራ ቬንትሪክል መስፋትን ወይም የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ መስፋትን ሊያሳይ ይችላል።

  የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በር አለመዘጋት የልብ የጤና ችግርን ለማከም በምግብ መልክ የሚወሰደውን የጨው መጠን መቀነስ ፣ ፈሳሽ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን (Diuretics) መጠቀም ፣ ከቬንትሪክል የሚረጨውን የደም ፍሰትን የሚገደብ ሃይልን ለመቀነስ የሚረዱ መድኃኒቶችን መጠቀም  እንዲሁም የካልሲየም ተቀባዩችን የሚዘጉ መድኒቶችን መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል። ከላይ በተጠቀሱት ህክምናዎች አጠጋቢ ውጤት በማይገኝበት ወይም በያአንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ከልብ የሚረጨው የደም መጠን በከፍተኛ ደረጃ በሚቀንስበት ወይም ቬንትሪክል በከፍተኛ ደረጃ በሚለጠጥበት ወቅት በቀዶ ጥቀና ህክምና የትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በርን በሌላ መቀየር  አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።