16.1.4.2. የፑልሞናሪ በር መዘጋት አለመቻል (pulmonary regurgitation)
የፑልሞናሪ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር ዋና መንስሄ በቀጥታ የፑልሞናሪ በር ላይ የሚፈጠር ጉዳት ወይም በልብ አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮችን ለማከም የሚደረግ የቀዶ ጥገና ህክምና በተደረገላቸው ህጻናት ላይ በፑልሞናሪ በር ላይ የሚፈጠር ጉዳት ነው። በተጨማሪም ለረጅም ግዜ በከፋ ሆኔታ ላይ የሚገኝ የፑልሞናሪ አርተሪ የደም ግፊት መጠን መጨመር የቀኝ ቬንትሪክል ከሚገባው መጠን በላይ እንዲለጠጥ በማድረግ የፑልሞናሪ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።
የቀኝ ቬንትሪክል ከሚገባው መጠን በላይ በሚወፍርበት እና በሚለጠጥበት ወቅት የፑልሞናሪ አርተሪ በር ላይ የሚገኙ ተከፋቾች ወይም ካስፒዶች ከመጠን በላይ ስለሚራራቁ እና የፑልሞናሪ በር ስለሚከፈት በፑልሞናሪ አርተሪ ውስጥ የነበረው ደም የቀኝ ቬንትሪክል በሚለጠጥበት ወቅት ተመልሶ ወደ ቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገባ ይሆናል። ወደ ቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ በሚገባው የደም መጠን የተነሳ በቬንትሪክል ውስጥ የሚኖረው የደም እና የግፊት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። የፑልሞናሪ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር በከፋ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት በቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ የሚፈጠረው ከፍተኛ ግፊት ወደ ቀኝ አትሪየም ቀጥሎም በትልልቆቹ የደም መልስ ቧንቧዎች ውስጥ የሚኖረው የደም ግፊት መጠን ይጨምራል።
የፑልሞናሪ አርተሪ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር በሚከሰትበት ወቅት ምንም ዓይነት ምልክት ሳያስከትል ለረጅም ግዜ ሊቆይ ይችላል። የፑልሞናሪ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር የከፋ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት የደካም ስሜት መሰማት ፣ የትንፋሽ ማጠር ፣ ምንም ምግብ ሳይበሉ የሆድ መነፋት ስሜት መሰማት እና የእግር ዕብጠት ሊከሰት ይችላል።
በአካላዊ ምርመራ ቬንትሪክል በሚለጠጥበት ወቅት በፑልሞናሪ በር ላይ የሚሰማ ጤነኛ ያለሆነ የልብ ምት ድምጽ ( diastolic murmur) የሚሰማ ይሆናል።
የፑልሞናሪ በር መዘጋት አለመቻል የልብ የጤና ችግር መከሰቱን ለማወቅ እንዲሁም መንስሄ የሆነውን ሆኔታ ለመለየት እና በፑልሞናሪ በር ላይ የሚደረሰውን የጉዳት ደረጃ ለማወቅ ከሚረዱ የምርመራ መንገዶች መካከል ፡ የኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ የቀኝ አትሪየም ወይም የቀኝ ቬንትሪክል መጠን መጨመርን ሊያሳይ ይችላል።
የደረት ራጅ ምርመራ የቀኝ አትሪየም እና የቀኝ ቬንትሪክል መጠን መጨመርን ሊያሳይ ይችላል። በኢኮካርዲዮግራም ምርመራ የፑልሞናሪ በርን መጠን እና ተግባሩን ማየት ፣ በቀኝ አትሪየም ፣ በፑልሞናሪ አርተሪ እነ በቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ የሚከሰተውን የግፊት መጠን ልዩነት ማወቅ ይችላል።