18.1. የልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ የመለጠጥ እና የልብ ክፍሎች መስፋት እንዲፈጠር የሚያደርግ የልብ ጡንቻ የጤና ችግር (Dilated cardiomyopathy)
የልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ መለጠጥን ተከትሎ የሚከሰት የልብ ክፍሎች ከመጠን በላይ መስፋት የልብ ጡንቻ በተገቢው መጠን መኮማተር እንዳይችል እና ለሰውነት የሚያስፈልግውን በቂ የደም መጠን እንዳይረጭ ያደርጋል። የልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ መለጠጥን ተከትሎ የሚከሰተው የልብ ክፍሎች መስፋት ብዙሁን ጊዜ የሚያጠቃው የግራ እና የቀኝ ቬንትሪክሎችን ሲሆን በሚያስከትለው ከፍተኛ የጤና ችግር የተነሳም ለልብ ንቅል ተከላ ህክምና (heart transplant) ከሚያደርሱ የልብ የጤና ችግሮች መካከል በዋና ምክንያትነት የሚጠቀስ የልብ የጤና ችግር ነው።
የልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ የመለጠጥ እና የልብ ክፍሎች መስፋት የልብ የጤና ችግር ትክክለኛ መንስሄ ብዙሁን ግዜ የሚታወቅ ባይሆንም ለዚህ የጤና ችግር አጋላጭ ናቸው ተብለው ከሚገመቱ ሆኔታዎች መካከል ዋንኞቹ የአልኮል መጠጥ በብዛት መውሰድ ፣ እርግዝና ፣ በልብ ጡንቻ ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን ( የተለያዩ ዓይነት የቫይረስ ኢንፌክሽኖች ) ፣ ለተለያዩ የቶክሲን እና የኬሚካል አይነቶች መጋለጥ (ኮባልት ፣ ሊድ እና አርሲኒክ) ፣ የተለያዩ ጸረ ካንሰር መድኃኒቶችን መጠቀም (ዶክሶሩቢሲን / doxorubicin ፣ ሳይክሎፎስፋማይድ / Cyclophosphamide እና ቪንክርስቲን / Vincristine የጸረ ካንሰር መድኃኒቶች) ፣ በሰውነት ውስጥ የሚመረቱ ኬሚካሎች (Metabolic products) መጠን መዛባት ( በደም ውስጥ የሚገኘው የፎስፌት መጠን መጨመር ፣ የካልሲየም እና የፖታሲየም መጠን መቀነስ ፣ በደም ውስጥ የሚገኘው ዩሪያ ናይትሮጂን መጠን መጨመር / uremia ) ዋንኞቹ ናቸው።
የልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ የመለጠጥ እና የልብ ክፍሎች መስፋት የልብ የጤና ችግር ጋር ተያይዞ በቬንትሪክል ጡንቻ ላይ በሚፈጠረው የጉዳት ደረጃ እና በተጉዳው የቬንትሪክል ክፍል ላይ በመመርኮዝ በሽተኞች ላይ ከሚፈጠረው የግራ ወይም የቀኝ ቬንትሪክል የልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ ምልክቶችን እና ለውጦችን ሊይሳዩ ይችላሉ።
የልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ መለጠጥ የልብን የኤሊከትሪክ እንቅስቃሴ ሥርዓት አፈጣጠርን እና የፍሰት ሂደትን ሊያስተጓጎል ስለሚችል ከልብ ምት መዛባት ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦችም ሊከሰቱ ይችላሉ።
በተጨማሪም የልብ ጡንቻ ከመጠን ባለፈ መጠን መለጠጥ እና የልብ ክፍሎች በልብ በሮች ላይ በሚያስከትለው ጉዳት የተነሳ የልብ በሮች በትክክል ተግባራቸውን ማከናወን አንዳይችሉ እክል በመፍጠር ደም ከቬንትሪክል ወደ አትሪየም በተቃራኒ አቅጣጫ እንዲመለስ ሊያደርግ ይችላል። በዚህም የተነሳ ከልብ የሚረጨው የደም መጠን እንዲቀንስ እና ወደ ሳንባ ወይም ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ከሚረጨው የደም መጠን መቀነስ ጋር በተገናኝ የሚፈጠሩ ምልክቶች እና ለውጦችም ሊከሰቱ ይችላሉ።
የልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ የመለጠጥ እና የልብ ክፍሎች መስፋት የልብ የጤና ችግር ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካክል አካላዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት የትንፋሽ ማጠር ፣ ተንጋለው በሚተኙበት ወቅት የትንፋሽ ማጠር ፣ አካላዊ ወይም አስፖርታዊ እንቅስቃሴን ማድረግ አለመቻል ፣ አጠቃላይ የሆነ የሰውነት ድካም ስሜት መሰማት ፣ ማሳል ፣ በእግር እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ዕብጠት መከሰት እና እራስን መሳት ዋንኞቹ ናቸው።
የተለያዩ የምርመራ መንገዶችን በመጠቀም በልብ ጡንቻ ላይ የሚከሰት ከመጠን በላይ መለጠጥ እና የልብ ክፍሎች መስፋት መከሰትን መለየት ወይም ማወቅ ይችላል።
የደረት ራጅ ምርመራ የልብ መጠን መጨመርን እና የፑልሞናሪ የደም ቧንቧዎች በደም መሞላትን እና መገታተርን (congestion) ሊይሳይ ይችላል። የኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ የልብ ምት መዛባት ወይም የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ሥርዓት መቋረጥ መኖሩን ሊያሳይ ይችላል።
የኢኮካርዲዮግራም ምርመራ የቬንትሪክል ጡንቻ መለጠጥ እና መስፋትን ፣ በአጠቃላይ የልብ ግድግዳ እንቅስቃሴ መቀነስን እና ደም በሚትራል በር በኩል በተቃራኒ አቅጣጫ ማለትም ከቬንትሪክል ወደ አትሪየም ተመልሶ ሲገባ ሊታይ ይችላል።
በካርዲያክ ካቴተራይዜሽን ( cardiac Catheterization) ምርመራ በመጠን የጨመረ ወይም የሰፋ እና በሚገባ መኮማተር የማይችል የቬንትሪክል ግግዳ እንዲሁም ደም በሚትራል በር በኩል በተቃራኒ አቅጣጫ ከቬንትሪክል ወደ አትሪየም ሲመለስ ሊታይ ይችላል።
ከልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ መለጠጥ ጋር በተገናኘ ከቬንትሪክል ጡንቻ መኮማተር አለመቻል የተነሳ ሊከሰት የሚችለውን የልብ ድካም በሚገባ ማከም አስፈላጊ ይሆናል። አንጂኦቴንሲን አንድን ወደ አንጂኦቲንሲን ሁለት የሚቀየረውን ኢንዛይም ተግባር የሚገድቡ መድኃኒቶችን (ACEI) ፣ የቤታ ተቀባይ በሮችን የሚዘጉ መድኃኒቶችን እንዲሁም ፈሳሽ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን በመጠቀም ከልብ ድካም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ምልክቶችን እንዲሁም የሞት አደጋን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይቻላል።
በተጨማሪም የልብ ምት መዛባትን ለማስተካከል የሚረዳ መሳሪያ (implantable defibrillators) በበሽተኛው ልብ ላይ በመግጠም ከልብ መዛባት ጋር በተገናኘ ሊከሰት የሚችልን ድንገተኛ የሞት አደጋ (sudden death) የመከሰት እድል መቀነስ ይቻላል።