Course Content
ምዕራፍ አሥራ አራት : በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች
0/16
ምዕራፍ አሥራ አምሥት : ከልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ የልብ የጤና ችግሮች (Cardiac electrical system abnormalities)
0/16
ምዕራፍ አስራ ሰባት : በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Valvular heart diseases)
0/16
ምዕራፍ ሃያ አንድ : የልብ ድካምበሽታ (Heart failure )
0/1
ምዕራፍ ሃያ ሦስት : በደም ቧንቧዎች ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (Vascular diseases)
0/22
በልብ እና በደም ቧንቧ ሥር ዓት ክፍሎች ውስጥ ሊፈጠሪ የሚችሉ የጤና ችግሮች (Pathology of Cardiovascular System)

21.  የልብ ድካምበሽታ  (Heart failure) 

    የልብ ድካም በሽታ በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት ውስጥ በሚፈጠሩ የተለያዩ የጤና ችግሮች የተነሳ የልብ ደምን የመቀብል ወይም የመርጨት አቅም መቀነስን ተክትሎ በየደቂቃው ከልብ የሚረጨው የደም መጠን መቀነስ እንዲሁም የደም በሳንባ እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ መከማቸት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ምልክቶች እና ለውጦች እንዲከሰቱ የሚያደርግ የልብ የጤና ችግር ነው። በሌላ አነጋገር የልብ ድካም ማለት ልብ ሰውነት የሚያስፈልገውን የደም መጠን መርጨት በማይችልበት ደረጃ መጉዳት ማለት ነው።

   ለልብ ድካም በሽታ መንስሄ ወይም አጋላጭ ሆኔታዎች ናቸው ተብለው ከሚገመቱ ሆኔታዎች መካከል ወደ ልብ ሴሎች ከሚደርሰው የኦክሰጂን መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚከሰት የከፋ የልብ የጤና ችግር ፣ የደም ግፊት መጠን መጨመር ፣ የልብ ጡንቻ ከመጠን በላይ መለጠጥ እና መስፋት  ፣ የልብ ጡንቻ በከፍተኛ መጠን መወፈር ፣ የልብ ጡንቻ መለጠጥ እና መኮማተር አለመቻል ፣ በረጅም ጊዜ በልብ ሽፋን ወይም ፔሪካርዲየም ላይ በሚከሰት ብግነት የተነሳ የፔሪካርዲየም  መወፈር እና መጠንከር ፣ በልብ በሮች ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ የልብ በር የጤና ችግሮች እና የመሳሰሉት የጤና ችግሮች ዋንኞቹ የልብ ድካም በሽታ እንዲከሰት የሚያደርጉ ሆኔታዎች ናቸው።

    የቀኝ የልብ ክፍል ያልተጣራ ደምን ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በመቀበል በፑሎሞናሪ አርተሪ በኩል ወደ  ሳንባ ይረጫል። የግራ የልብ ክፍል ደግም በፑሎሞናሪ ቬን በኩል የተጣራ ደምን ከሳንባ በመቀብል ወደ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ይረጫል። የቬንትሪክል መኮማተር (ventricular contraction) ደምን በከፍተኛ ግፊት በመርጨት ደምን ከልብ እንዲወጣ በሚያደርጉ የደም ቧንቧዎች በኩል ክልብ እንዲወጣ የሚያደርግ ሲሆን የቬንትሪክል መለጠጥ (ventricular diastole) ደግሞ ደምን ከአትሪየም እንዲቀብል ያስችለዋል።

  የልብ ደምን የመርጨት አቅም የሚለካው በያንድ  አንዱ ደቂቃ ከልብ በሚረጨው የደም መጠን መሰረት ነው። በያንድ አንዱ ደቂቃ ከልብ የሚረጨው የደም መጠን ደግሞ በያንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ከቬንትሪክል በሚረጨው የደም መጠን እና በየደቂቃው በሚኖረው የልብ ምት ፍጥነት ላይ የሚወሰን ይሆናል። 

   የልብ አጠቃላይ ተግባር ወይም ደምን የመርጨት አቅም በሦስት ዋና ሆኔታዎች ላይ የሚወሰን ይሆናል። እነዚህም ሦስት ሆኔታዎች ቬንትሪክል ከመኮማተሩ በፊት በቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን (preload) ፣ የቬንትሪክልን የደም የመርጨት ተግባር የሚገዳደር ሃይል መጠን (after load)  እና የልብ ጡንቻ የመኮማተር አቅም (contractility) ናቸው።

ቬንትሪክል ከመኮማተሩ በፊት በቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን ማለት በቬንትሪክል የመለጠጥ ሂደት መጨረሻ ላይ በቬንትሪክል ውስጥ የሚጠራቀመው የደም መጠን ማለት ሲሆን ቬንትሪክል ከመኮማተሩ በፊት በቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን በሚጨምርበት ወቅት ደምን ወደ ልብ በሚያደርሱ የደም ቧንቧዎች ወይም የኮሮናሪ አርተሪዎች ውስጥ የሚኖረው የግፊት መጠን እንዲሁም በቬንትሪክል ግድግዳ ላይ የሚፈጠረው የግፊት መጠን የሚጨምር ይሆናል። ይህም በያአንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ከልብ የሚረጨው የደም መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። 

  የቬንትሪክልን የደም የመርጨት ተግባር የሚገዳደር ሃይል ወይም ከቬንትሪክል የሚረጨውን የደም ፍሰት የሚገድብ ሃይል ማለት ቬንትሪክል ደምን ለመርጨት የሚጠቀመውን የግፊት ሃይል ለመቋቋም የሚፈጠር የግፊት ሃይል ሲሆን ይህም በደም ቧንቧዎች በተለይም በደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ውስጥ ከሚፈጠረው የግፊት መጠን ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅነት ያለው ነው። በደም ቅዳ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚገኘው የግፊት መጠን በሚጨምርበት ወቅት የቬንትሪክልን የደም የመርጨት ተግባር የሚገዳደር ሃይል መጠን የሚጨምር እና ከልብ የሚረጨው የደም መጠን የሚቀንስ ይሆናል።

  ቬንትሪክል ከመኮማተሩ በፊት በቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን መጨመር ፣ የቬንትሪክልን የደም የመርጨት ተግባር የሚገዳደረው ሃይል መጠን ዝቅተኛ መሆን እና የልብ ጡንቻ የመኮማተር አቅም ከፍተኛ መሆን የልብ ደምን የመርጨት አቅም አንዲጨምር የሚያደርጉ ሆኔታዎች ናቸው። በተቃራኒው ቬንትሪክል ከመኮማተሩ በፊት በቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን መቀነስ ፣ የቬንትሪክልን የደም የመርጨት ተግባር የሚገዳደር ሃይል መጠን ከፍተኛ መሆን ወይም  የልብ ጡንቻ የመኮማተር አቅም መቀነስ የልብ ደምን የመርጨት አቅም እንዲቀንስ የሚያደርጉ ሆኔታዎች ናቸው።

   ቬንትሪክል ከመኮማተሩ በፊት በቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን ዝቅተኛ በሚሆንበት እንዲሁም የቬንትሪክልን የደም የመርጨት ተግባር የሚገዳደር ሃይል መጠን ከፍተኛ በሚሆንበት ወቅትም እንኳን ቢሆን የልብ የመኮማተር አቅም መጨመር ለሰውነት የሚያስፈልገውን የደም መጠን ለማሟላት ከልብ የሚረጨው የደም መጠን እንዲጨምር በማድረግ ረገድ  የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። የልብ የመኮማተር አቅም በቂ የሆነ ኦክስጂን ፣ የሃይል ምንጭ እና ካልሲየም የሚያስፈልገው ተግባር ነው። በተጨማሪም የልብ የመኮማተር ወይም የልብ አጠቃላይ ተግባር በሲምፓተቲክ እና በፓራሲምፓተቲክ የነርቭ ሥርዓት ቁጥጥር ሥር ሆኑ የሚተገበር ሂደት ነው።

   በአጠቃላይ ቬንትሪክል ከመኮማተሩ በፊት ወደ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን መቀነስ ፣ ከቬንትሪክል የሚረጨው የደም ፍስትን የሚገድብ ሃይል መጨመር ወይም የልብ የመኮማተር አቅም መቀነስ እንዲከሰት የሚያድርጉ ሆኔታዎች በያንድ አንዱ ቬንትሪክል መኮማተር ወቅት የሚረጨውን የደም መጠን በመቀነስ ወይም ለተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚደረሰው የደም መጠን እንዲቀነስ በማድረግ የልብ ድካምበሽታ (Heart failure) እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ። 

  የልብ ድካም በሽታ ከልብ በሚረጨው የደም መጠን ሆኔታ ፣ ለልብ ድካም በሽታ መንስሄ በሆነው ወይም ጉዳት በደረሰበት የልብ ክፍል እንዲሁም ጉዳት በደረሰበት የልብ ተግባር መሰረት በተለያዩ ምድቦች ሊከፋፈል ይችላል።

  የልብ ድካም በሽታ ሁልገዜ ከልብ ከሚረጨው የደም መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ ብቻ የሚፈጠር የጤና ችግር አይደለም። አንድ አንድ ግዜ ከልብ የሚረጨው የደም መጠን በሚጨምርበት ነገር ግን በዚህ ከልብ በሚረጨው ከፍተኛ መጠን ያለው ደም የሰውነት ፍላጎትን ማሟላት በማይቻልበት ወቅትም የልብ ድካም በሽታ ሊፈጠር ይችላል። ስለሆነም የልብ ድካም በሽታ ወደ ልብ ከሚገባው የደም መጠን ወሰጥ ከልብ የሚረጨው የደም መጠን መጨመር ወይም ከልብ የሚረጨው የደም መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ ሊከሰት ይችላል።

   ወደ ልብ ከሚገባው የደም መጠን ውስጥ ከልብ የሚረጨው የደም መጠን መጨመር ጋር በተያያዘ የሚከሰት የልብ ድካምበሽታ (high output failure) እንዲፈጠር ሊያደርጉ ከሚችሉ ሆኔታዎች መካከል የደም ማነስ ፣ የታይሮይድ ሆርሞን ከመጠን በላይ መመረት እንዲሁም በአርተሪ እና በቬን መካከል ያልተገባ ግንኙነት መፈጠር ዋንኞቹ ሆኔታዎች ናቸው። 

   ወደ ልብ ሴሎች ከሚደርሰው የደም ወይም የኦክሰጂን መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚከሰት የከፋ የልብ የጤና ችግር (MI) ፣ በፔሪካርዲየሞች መካክል በሚገኘው ክፍተት ውስጥ የሚገኘው ፈሳሽ የልብን ተግባር በሚገድብ መጠን መጨመር (cardiac tamponade) ፣ በጥንድ የሳንባ ሽፋን መካከል በሚገኘው ክፍተት ውስጥ አየር መከማቸት (tension pneumothorax) ፣ የፑልሞናሪ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚፈጠር የደም መርጋት ወይም ከሌሎች የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በሚነሱ የደም መርጋት ስብርባሪዎች መዘጋት (pulmonary embolism) ፣ በፍጥነት የሚከሰት በልብ በሮች ላይ የሚፈጠር ጉዳት እና የመሳስሉት ሆኔታዎች ወደ ልብ ከሚደርሰው የደም መጠን ወሰጥ ከልብ የሚረጨው የደም መጠን መቀነስ ጋር በተያያዘ የሚከሰት የልብ ድካም (low output failure)  እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሆኔታዎች ናቸው።

    እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ውስጥ የደም ማነስ በሽታ በተለይም በእርጉዝ ሴቶች እና በእድሜ በገፉ ሰዎች ላይ ዋና የልብ ድካም በሽታ እንዲፈጠር የሚያደርግ የጤና ችግር ነው። በተጨማሪም እንደ ወባ ፣ የደም ካንሰር የጤና ችግሮች ፣ የመቅኔን ተግባር የሚገድቡ ጸረ – ካንሰር እና ሌሎች መድኃኒቶች እንዲሁም  ሌሎች የቀይ የደም ሴሎችን የሚያጠቁ የጤና ችግሮች የከፋ ደረጃ ላይ የደረስ የደም ማነስ የጤና ችግር (sever anemia) እንዲከሰት በማድረግ የልብ ድካም በሽታ እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።  

 በእርግዝና ወቅት የሚፈጠር የደም ማነስ ወይም በወሊድ ወቅት ከሚከሰት የደም መፍሰስ ጋር በተገናኘ ከሚፈጠር የደም ማነስ የተነሳም የልብ ድካም የልብ የጤና ችግር ሊክሰት ይችላል። 

በቬንትሪክል የመለጠጥ እና የመኮማተር በቃት ላይ በመመሰረት የልብ ድካም በሽታ ከቬንትሪከል የመኮማተር አቅም መቀነስ ጋር በተገናኘ ወይም ከቬንትሪክል የመለጠጥ አቅም መቀነስ ጋር በተገናኘ ሊከሰት ይችላል። 

    ከቬንትሪክል መኮማተር አቅም መቀነስ ጋር በተያየዘ የሚፈጠር የልብ ድካምበሽታ (Systolic HF) የሚከሰተው ወደ ቬንትሪክል ውስጥ ከሚገባው የደም መጠን ውስጥ በያንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ከቬንትሪክል የሚረጨው የደም መጠን እንዲሁም  በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በኩል ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚረጨው የደም መጠን እንዲቀንስ በሚያደርጉ የጤና ችግሮች የተነሳ ነው።

 ከቬንትሪክል የመለጠጥ አቅም መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ ድካምበሽታ (Diastolic heart failure) ደግሞ የሚፈጠረው ወደ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን እንዲቀንስ እንዲሁም ደምን ወደ ልብ በሚመልሱ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚጠራቀመው የደም መጠን እንዲጨምር በሚያደርጉ የተለያዩ የጤና ችግሮች የተነሳ ነው።

  ከቬንትሪክል መኮማተር አቅም መቀነስ ጋር በተያየዘ የሚፈጠር የልብ ድካም ወደ ቬንትሪክል ውስጥ ከሚገባው የደም መጠን ውስጥ በያአንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ወቅት ከቬንትሪክል የሚረጨው የደም መጠን ወይም ኢጂክሽን ፍራክሽን (Ejection Fraction / EF) እንዲቀንስ ያደረጋል። ከቬንትሪክል መኮማተር አቅም መቀነስ ጋር በተያየዘ የሚፈጠር የልብ ድካም በሽታ ቬንትሪክል ሙሉ ለሙሉ ከተለጠጠ በኋላ በቬንትሪክል ውስጥ የሚጠራቀመው የደም መጠን ወይም ቬንትሪክል ከመኮማተሩ በፊት በቬንትሪክል ውስጥ የሚጠራቀመው የደም መጠን እና ቬንትሪክል ከተኮማተረ በኋላ በቬንትሪክል ውስጥ የሚቀረው የደም መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። ይህ በቬንትሪክል ውስጥ የሚጨምረው የደም መጠን ወደ አትሪየም ከዚያም በሳንባ እና በልብ መካከል በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ በመሰራጨት በልብ እና በሳንባ መካከል በሚገኙ የደም ቧንቧዎች እንዲሁም በሳንባ ውስጥ የሚጠራቀመው የፈሳሽ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።

  ከቬንትሪክል የመለጠጥ አቅም መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ ድካም የቬንትሪክል ግድግዳ በተገቢው መጠን እንዳይለጠጥ እና ቬንትሪክል በሚያስፈልገው መጠን ከአትሪየም በሚመጣው ደም እንዳይሞላ በሚያደርጉ የጤና ችግሮች የተነሳ የሚፈጠር የልብ ድካም በሽተ ዓይነት ነው። የቬንትሪክል ግድግዳ በተገቢው መጠን እንዳይለጠጥ ከሚያደርጉ የጤና ችግሮች መካከል የልብ ግድግዳ ከሚገባው መጠን በላይ መወፈር ፣ ከእድሜ መጨመር ጋር በተገናኘ የልብ ግድግዳ  የመለጠጥ አቅም መቀነስ ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የቬንትሪክል ጡንቻ ከሚገባው በላይ እንዲለጠጥ እና እንዲሰፋ የሚያደርጉ የጤና ችግሮች ወይም ወደ ልብ ሴሎች የሚደረሰው የደም ወይም የኦክስጂን መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚከሰት የከፋ የልብ የጤና ችግር ዋንኞቹ ናቸው።

    የልብ ድካም በሽታ ጉዳት ከደረሰበት የልብ ክፍል ጋር በተገናኘ በቀኝ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ በሚከሰት የጤና ችግር የተነሳ የሚፈጠር የልብ ድካምበሽታ (right sided HF) እና በግራ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ በሚከሰት የጤና ችግር የተነሳ የሚፈጠር የልብ ድካም በሽታ (left sided HF)  በመባል በሁለት ሊከፈል ይችላል።

   በግራ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ ድካም በሽታ የግራ ቬንትሪክል ደምን የመርጨት አቅምን በመቀነስ ደም በግራ ቬንትሪክል ወደ ግራ አትሪየም ከዚያም በሳንባ እና በልብ መካከል ወደሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ ተመልሶ እንዲገባ በዚህም በሳንባ ውስጥ ፈሳሽ መጠራቀም እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።

       በግራ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ ድካም  ከልብ በየደቂቃው ከቬንትሪክል የሚረጨው የደም መጠን ወይም ወደ ተለያዩ የሰወነት ክፍሎች የሚረጨው የደም መጠን እንዲቀንስ እንዲሁም በልብ እና በሳንባ መካከል በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚከማቸው የደም መጠን እንዲጨምር የሚያደርግ የልብ ድካም ዓይነት ነው። በግራ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚፈጠረው የልብ ድካም በሽታ ወደ ቬንትሪክል ውስጥ ከሚገባው የደም መጠን ውስጥ በያአንድ አንዱ የቬንትሪክል መኮማተር ውቀት የሚረጨው የደም መጠን እንዲቀንስ ወይም ከሚጠበቀው መጠን በታች እንዲሆን ያደርጋል። በተጨማሪም በግራ ቬንትሪክል እና አትሪየም ውስጥ የሚገኘው የግፊት መጠን የሚጨምር እና በሳንባ ውስጥ ፈሳሽ እንዲጠራቀም ሊያደርግ ይችላል። 

  በግራ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ ድካም በሽታ እንዲከሰት ሊያድርጉ ከሚችሉ የጤና ችግሮች መካከል የደም ግፊት መጠን መጨመር ፣ በልብ በሮች ላይ የሚፈጠሩ ጉዳቶች እንዲሁም ወደ ልብ ሴሎች የሚደረሰው የደም እይም የኦክሰጂን መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚከሰት የከፋ የልብ የጤና ችግሮች ዋንኞቹ ናቸው።

 በቀኝ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ ድካም የግራ ቬንትሪክል የደም የመርጨት አቅም መቀነስን ተከትሎ ወደ ግራ አትሪየም ፣ የፑልሞናሪ የደም ቧንቧዎች ውስጥ ከሚተላለፈው የገፊት እና የፈሳሽ መጠን መጨመር ጋር በተገናኘ ሊፈጠር ይችላል። በዚህም ከቀኝ ቬንትሪክል ወደ ሳንባ የሚረጨው የደም መጠን እንዲሁም ወደ ቀኝ የልብ ከፍል ውስጥ የሚገባው የደም መጠን እንዲቀንስ በማድረግ ወደ ልብ የሚመለሰው ደም በሆድ አቃ ፣ በጉበት እና  በእግር ውሰጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ እንዲጠራቀም በዚህም በእነዚህ  የሰውነት ክፍሎች ውስጥ የሚፈጠር ዕብጠት እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል።

   በቀኝ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ ድካም በሽታ የቀኝ የቬንትሪክል የመኮማተር አቅም እንዲቀንስ በማድረግ በቀኝ ቬንትሪክል እና በአትሪየም ውስጥ የሚኖረው የደም እና የግፊት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል። ይህም ግፊት ደምን ወደ ልብ በሚመልሱ የደም ቧንቧዎች ወይም በትልልቆቹ የደም መልስ ቧንቧዎች ፣ በሆድ እቃ ፣ በጉበት እና በእግር ውስጥ በመሰራጨት በተጠቀሱት የሰውነት ክፍሎች ውስጥ የሚከማቸው የፈሳሽ መጠን እንዲጨምር እና የሰውነት ዕብጠት እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል። 

   በቀኝ በኩል በሚገኘው የልብ ክፍል ላይ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የልብ ድካም በልብ እና በሳንባ መካከል በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ የሚኖረው የደም ግፊት እና የፈሳሽ መጠን እንዲጨምር ሊያደርግ አይችልም።

    ከልብ ወደተለያዩ የሰውነት ከፍሎች የሚረጨው የደመ መጠን የሰውነትን ፍላጎት ማሟላት በማይችልበት ወቅት ሰውነት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የተፈጠረውን ችግር ለማስተካከል ጥረት ያደረጋል። ከልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ ሰውነት የተፈጠረውን ሆኔታ ለማሰተካከል በሚያደርገው ጥረት ሂደት ውስጥ የተለያዩ ምልከቶች እና ለውጦች የሚፈጠሩ ይሆናል። 

   ከልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦች በዋናነት የሚከሰቱት በሦስት የተለያዩ ምክንያቶች ነው። የልብ ደምን የመርጨት አቅም መቀነስን ተከትሎ በልብ ጡንቻ ላይ የሚፈጠሩ ለውጦች ፣ ወደ ኩላሊት ከሚደርሰው የደም መጠን መቀነስን ተከትሎ በኩላሊት ፣ በሌሎች ዕጢዎች እና የሰውነት ክፍሎች በሚመረቱ ሆርሞኖች (የሪኒን –  አነጂኦቲንሲን – አልዶስቲሮን ሥርዓት )እንዲሁም በደም ቧንቧዎች ውሰጥ ከሚፈጠረው የግፊት መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የሚፈጠረው የሲምፓተቲክ የነርቭ ሥርዓት መነቃቃት ዋንኞቹ ክልብ ድካም ጋር በተገናኙ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ምክንያቶች  ናቸው።

ክልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል በደም ቧንቧዎች ከሚጠራቀመው ፈሳሽ እና የሪኒን አንጂኦቲንሲን – አልዶስቲሮን ሥርዓት መነቃቃት የተነሳ በተለያያዩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ የሚኖረው የፈሳሽ መጠን መጨመር ወይም የሰውነት ዕብጠት ፣ የትንፋሽ ማጠር ፣ የድካም ስሜት ፣ በጣት እና በከንፈር አካባቢ የሚገኘው የቆዳ ቀለም መቀየር ፣ የሰውነት ጡንቻ መክሳት ፣ በሽታው እየከፋ ሲመጣ ወደ አንጎል ከሚደርሰው የደም ወይም ኦክሰጂን መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የአይምሮ መዘባረቅ ፣ በሰውነት ውስጥ ከሚፈጠረው የፈሳሽ መጠን መጨመር ጋር በተገናኘ የሚፈጠር የደም ማነስ ፣ የልብ ምት መዛባት እና በድንገት የሚከሰት የሞት እደጋ ሊከሰት ይችላል።

  በተጨማሪም ከልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ በልብ እና በሳንባ መካከል በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውስጥ ከሚፈጠር የፈሳሽ እና የግፊት መጠን መጨመር የተነሳ በሳንባ ውስጥ በሚጠራቀም ፈሳሽ የተነሳ በፍጥነት የሚከሰት ለህይውት አደገኛ የሆነ ሆኔታ ሊፈጠር ይችላል። በሳንባ ውስጥ ከሚፈጠር የፈሳሽ መጠራቀም ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል በደም ውስጥ የሚገኘው የኦክስጂን መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ፣ የትንፋሽ ማጠር ፣ በየደቂቃው ከልብ የሚረጨው የደም መጠን መቀነስ ፣ በሚተኙበተ‍እ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለወወ ትራሰወ መጠቀም ፣ ተንጋለው በሚተኙበት ወቅት የሚከሰት የትንፋሽ ማጠር ፣ ከእንቅልፍ የሚቀሰቀስ በተደጋጋሚ የሚፈጠር ማሳል ፣  ወደ አንጎል ከሚደርሰው የደም ወይም የኦክሰጂን መጠን መቀነስ ጋር በተገናኘ የአይምሮ መዘበራረቅ ፣ ደም የቀላቀለ እክታ እና ሳል እንዲሁም በስንባ ውስጥ የሚሰማ ተጨማሪ ድምጽ የመሳለሉት ሆኔታዎች ከልብ ድካም ጋር በተገናኘ በሳንባ ውስጥ የሚጠራቀም ፈሳሽ በሚፈጠርበት ወቅት የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦች ናቸው።

   የልብ ድካም በሽታ መከሰቱን እንዲሁም የተከሰተውን የልብ ድካም በሽታ ደረጃ እና መንስሄ ለማወቅ ከበሽተኛው የሚወሰደውን የበሽታውን ታሪክ ፣ ከአካላዊ ምርመራ የሚገኘውን ውጤት እንዲሁም ሌሎች የላብራቶሪ እና የልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት ክፍሎችን ሊያሳዩ የሚችሉ የምርመራ መንገዶችን መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል።  በአካላዊ ምርመራ የልብ ምት ፍጥነት መጨመር ፣ ተጨማሪ የልብ ምት ድምጽ መሰማት ፣ በደም ውስጥ የሚገኘው የኦክስጂን መጠን መቀነስን የሚያመለክት በጣት እና በከንፈር አካባቢ በሚገኘው ቆዳ ላይ የቀለም ለውጥ መታየት ፣ የደም ግፊት መጠን መጨመር ወይም መቀነስ ፣ በአንገት አካባቢ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች መገታተር እንዲሁም በእግር ላይ የሚከስት ዕብጠት በብዛት ከልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ በአካላዊ ምርመራ የሚገኙ ውጤቶች ናቸው። 

   በላብራቶሪ ምርመራ የደም ማነስ ወይም በሰውነት ፈሳሽ ውስጥ የሚገኙ ነጥረ ነገሮች ( ኤሌክትሮላይቶች) መጠን እና ይዘት መዛባት ሊታይ ይችላል። የደረት ራጅ ፣ የኤሌክትሮካርዲዮግራም  እና የኢኮካርዲዩግራም ምርመራዎች የልብ ድካም በሽታ መከሰቱን እንዲሁም መንስሄ የሆነውን ሆኔታ ለመለየት የሚረዱ የምርመራ መንገዶች ናቸው።

   ለልብ ድካም በሽታ የሚሰጡ የህክምና መንገዶች የልብ ድካም በሽታው በሚገኝበት ደረጃ እና ለልብ ድካም በሽታ መንስሄ በሆነው ሆኔታ ላይ የሚወስን ሲሆን በአጠቃላይ ህክምናው በመድኃኒት መልክ የሚሰጥ ወይም ከመድኃኒት ውጭ የሚሰጥ ህክምና ተብሎ ሊከፈል ይችላል።

ለልብ ድካም በሽታ መንስሄ የሆነውን ሆኔታ ከማስወገድ በተጨማሪ ከልብ ድካም በሽታ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶችን እና ለውጦችን ለመቆጣጠር  ከሚሰጡ ህክምናዎች መካከል በቂ የሆነ አካላዊ አንቅስቃሴ ማድረግ ፣ በምግብ እና በመጠጥ መልክ ወደ ሰውነት የሚገባውን የጨው መጠን መቀነስ እንዲሁም ወደ ሰውነት የሚገባውን የፈሳሽ መጠን መወሰን ወይም መቆጣጠር ዋንኛ የልብ ድካምን ያለ መድኃኒት ለማከም የሚረዱ ሆኔታዎች ናቸው።  

   ፈሳሽ ከሰውነት እንዲወገድ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን ፣ የልብ የመኮማተር አቅም እንዲጨምር የሚያደርጉ መድኃኒቶችን ፣ እንጂቲንሲን አንድን ወደ አንጂኦቲንሲን ሁለት የሚቀየረውን ኢንዛይም ተግባር የሚገድቡ መድኃኒቶችን ፣ የቤታ ተቀባዩችን የሚገድቡ መድኃኒቶችን እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ኦክስጂንን መጠቀም በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ ከልብ ድካም ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶቸ‍ን እና ለውጦችን ለመቆጣጠር የሚረዱ የመድኃኒት ዓይነቶች ናቸው። እነዚህን መድኃኒቶች የመጠቀም ሆኔታ ለልብ ድካም በሽታ መንስሄ በሆነው ሆኔታ ላይ እና መንስሄ በሆነው የልብ ክፍል ላይ የተመሰረተ ይሆናል። 

   በተጨማሪም የልብን የኤሌክትሪክ እንቅሰቃሴ ሥርዓት በመቆጣጠር የልብ ምት መዛባትን የሚገድቡ መድኃኒቶችን እና መሳሪያዎችን በመጠቀም እንዲሁም በሽታው የከፋ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ደግሞ ሌሎች የህክምና መንገዶችን ጨምሮ የልብ ንቅለ ተከላ ህክምና አሰፈላጊ ሊሆን ይችላል።