22. በልብ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚከሰት ኢንፌክሽን ወይም ብግነት (Infectious heart disease)
በልብ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚከሰት ኢንፌክሽን ወይም ኢንፌክሽንን ተከትሎ በሚነቃቃው የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት የተነሳ በልብ ክፍሎች ላይ የሚፈጠር ብግነት (Endocarditis) በደም ዝውውር ሥርዓት ውስጥ ደም በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲፈስ እና ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ እንዳይመለስ በሚከላከሉ በልብ በሮች ፣ በልብ የውስጠኛ ግድግዳ ክፍል ፣ በልብ ጡንቻ እንዲሁም በልብ ሽፋን ላይ በኢንፌክሽን – አምጭ ተህዋሲያን የተነሳ የሚፈጠር ኢንፌክሽን ወይም የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት በተለያዩ የልብ ከፍሎች ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት ወይም ብግነት የተነሳ የሚፈጠር የጤና ችግር ነው። በልብ የውሰጠኛ ከፍሎች ላይ የሚፈጠር ኢንፌክሽን ወይም ብግነት ብዙሁን ግዜ የሚከሰተው በተደጋጋሚ በስትሪፕቶኮካል ባክቲሪያ ኢንፌክሽን በሚጠቁ ሰዎች ፣ የሰው ሰራሽ የልብ በር በተገጠመላቸው ሰዎች ፣ በሰውነት ውስጥ በተሰራጨ ኢንፌክሽን በተጠቁ ሰዎች ፣ ደካማ የሰውነት የበሽታ የመከላክል አቅም ባላቸው ሰዎች ወይም በልብ እና በደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቅት በሚከሰቱ የልብ የጤና ችግሮች በተጠቁ ሰዎች ላይ ነው።
በልብ በሮች ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን ጤነኛ የልብ በሮች ባሏቸው ሰዎች ላይ የመከሰት እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። በልብ ውስጥ እንዲሁም በልብ እና ከልብ በሚነሱ የደም ቧንቧዎች መካከል የሚኖረውን ፍሰት የሚገድቡ የልብ በሮች (የልብ በሮች መጥበብ) ፣ደም በተቃራኒ አቅጣጫ እንዳይፈስ መገደብ ወይም መከላከል የማይችሉ በሮች (የልብ በሮች መዘጋት አለመቻል) ፣ በደም ሥር የሚወሰዱ አደንዛዥ ወይም አነቃቂ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች ፣ በአፍ ውስጥ በድድ ኢንፌክሽን የሚጠቁ ሰዎች ፣ የበሽታ መከላኪያ አቅምን የሚቀንሱ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች እንዲሁም በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ የቀዶ ጥገና ህክምና ያደረጉ ሰዎች በልብ በሮች ላይ ለሚከሰት ኢንፌክሽን ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
በልብ የውስጠኛ ግድግዳ ፣ በልብ በሮች ፣ በልብ ጡንቻ እንዲሁም በልብ ሽፋን ወይም ፔሪካርዲየም ላይ ከሚፈጠር ኢንፌክሽን ወይም ብግነት የተነሳ ሊከሰቱ ከሚችሉ የጤና ችግሮች መካከል በልብ የውስጥ ግድግዳ ክፍሎች እና በልብ በሮች ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን (infective endocarditis) ፣ ከስትሪፕቶኮካል የጉሮሮ ኢንፌክሽን ጋር በተገናኘ በሰውነት የበሽታ መከላኪያ ፕሮቲን የተነሳ በልብ በሮች ላይ የሚከሰት የልብ የጤና ችግር ( Rheumatic Heart Disease / RHD) ፣ በልብ ጡንቻ ላይ የሚፈጠር ኢንፌክሽን ወይም ብግነት (myocarditis) እንዲሁም በልብ ሽፋን ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን ወይም ብግነት (pericarditis) ዋንኞቹ በልብ የተለያዩ ክፍሎች ላይ የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች ወይም ብግነቶች ናቸው