23.2.2. በአንጎል ውስጥ ከሚፈጠር የደም መፍሰስ ጋር በተገናኘ የሚከሰት ስትሮክ (hemorrhagic stroke)
በአንጎል ውስጥ ከሚፈጠር የደም መፍሰስ ጋር በተገናኘ የሚከሰት ስትሮክ (hemorrhagic stroke) በጣም አደገኛው የስትሮክ ዓይነት ሲሆን የሚፈጠረውም በአንጎል ውስጥ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በሚከሰት ጉዳት የተነሳ በአንጎል ውሰጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ የሚፈጠር መሸንቆርን ፣ መቀደድን ወይም መፈንዳትን ተከትሎ በአንጎል ክፈሎች ውሰጥ የደም መፍሰስ በሚፈጠርበት ወቅት ነው።
በአንጎል ወሰጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ የሚፈጠር መሸንቆርን ፣ መቀደድን ወይም መፈንዳትን ተከትሎ በአንጎል ክፍሎች ውስጥ የሚፈሰው ደም በአንጎል ውስጥ በመጠራቀም እና የአንጎል ክፍሎችን በመጨፍልቅ በአንጎል ክፍሎች እና ሴሎች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ይሆናል። በጭንቅላት ቅል ውስጥ የሚገኘው ክፍል ከአንጎል ክፍሎች ፣ አንጎል ከሚዋኝበት ፈሳሽ ወይም የአንጎል እና ህብለሰረሰር ፈሳሽ (cerebrospinal fluid) እና በጭንቅላት ቅል ውስጥ ከሚገኙ የደም ቧንቧዎች ውጭ ሌላ ተጨማሪ ነገር መጨመር እና መያዝ አይችልም። ስለሆነም በአንጎል ውስጥ ደም በሚፈስበት ወቅት በአንጎል ክፍሎች ላይ ቀጥተኛ ጫና ከማድረጉ በተጨማሪ የተወሰነውን የአንጎል ክፍል በጭንቅላት ቅል ውስጥ በሚገኙ ቀዳዳዎች ውስጥ እንዲሰነቀር ወይም የተወሰነ የአንጎል ክፍል እንዲጨፍለቅ በማድርግ በማህከላዊ የነርቭ ሥርዓት ላይ በሚያሳድረው ተጽህኖ የተነሳ በፍጥነት የሞት አደጋ ሊያስከትል የሚችል የስትሮክ ዓይነት ነው።
የደም ግፊት መጠን መጨመር በሽታ ፣ የእድሜ መግፋት ፣ በአንጎል ውስጥ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች ግድግዳ መሳሳት ፣ መለጠጥ እና መሰርጎድ (aneurysm) ፣ በደም ቧንቧ አፈጣጠር ሂደት ወቅት በሚከሰት አክል የተነሳ የሚፈጠር የደም ቧንቧዎች ጉድለት (malformation) ፣ በአንጎል ውስጥ በሚገኙ የደም ቅዳ ቧንቧ እና የደም መልስ ቧንቧ መካከል ያልተገባ ግንኙነት መፈጠር ( arteriovenous malformation) ፣ በጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠሩ ካንሰሮች ፣ በአንጎል ውስጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ የሚፈጠር ብግነት ፣ በደም መርጋት ሥርዓት ላይ የሚፈጠር የጤና ችግር (bleeding disorders) እንዲሁም ደም እንዲቀጠን የሚያደርጉ መድኃኒቶችን መጠቀም በአንጎል ውስጥ ለሚፈጠር የደም መፍሰስ የጤና ችግር ሊያጋልጡ የሚችሉ የጤና ችግሮች ወይም ሆኔታዎች ናቸው። ከላይ የተገለፁት ሆኔታዎች ወይም የጤና ችግሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መነግድ በአንጎል ወሰጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ላይ በሚያስከትሉት ጉዳት ወይም ተፅህኖ የተነሳ የደም ቧንቧ መሽንቆር ፣ መቀደድ ወይም መፈንዳት እንዲፈጠር በማደረግ በአንጎል ክፍሎች ወሰጥ የሚከሰት እና የደም መፍሰስ እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።
በአንጎል ክፍሎች ወሰጥ በሚፈጠር የደም መፍሰስ የተነሳ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል ከፍተኛ የሆነ የራስ ምታት (በህይወት ለመጀመሪያ ግዜ ከፍተኛ የሆነ የራስ ምት) ፣ ማስታወክ ፣ የደም ፍሰት ከተከሰተበት የአንጎል ክፍል በተቃራኒ የሚገኘው የሰውነት ክፍል መዛል እና መታዘዝ አለመቻል ፣ በአንጎል ውስጥ ከሚፈሰው ደም የተነሳ በአንጎል ክፍሎች ላይ በሚፈጠር ጫና ምክንያት የአንጎል ሴሎች ዕብጠት ፣ የተወሰነ የአንጎል ክፍል በጭንቅላት ቅል ውስጥ በሚገኝ ክፍት ክፍል ውስጥ መሰንቀር ወይም አንድ የተወሰነ የአንጎል ክፍል ባልተገባ ሆኔታ የጭንቅላት ክፍል ውስጥ መገኘት (cerebral herniation) ፣ እራስን መሳት እንዲሁም በፍጥነት የሚከሰት ሞት ሊያስከትል ይችላል።