ለ) የቡርገር በሽታ (Buerger’s disease) ወይም የትሮምቦአንጃይቲስ ኦብሊትራንስ በሽታ (Thromboangiitis Obliterans)
ሌላኛው በመካከለኛ እና በትንንሽ መጠን ባላቸው የደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ በተለይም በእጅ እና በእግር ውስጥ በሚገኙ የደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ ብግነት ወይም ቁስለት እንዲፈጠር የሚያደርግ የጤና ችግር ነው። በቡርገር በሽታ የተጠቁ የደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ የመቁሰል ፣ የማበጥ ፣ የመጠበብ እና የመዘገታ አደጋ ሊፈጠር ይችላል። ይህም ሆኔታ ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች ፣ ለደም ፍሰት መቀነስ ወይም መቋርጥ ሊዳረግ ይችላል።
የቡርገር በሽታ መንስሄ በትክክል አይታወቅም። ለዚህ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ አጋላጭ ተደርጎ የሚታወቀው ሲጋራ ማጤስ ነው። ስለሆነም ሲጋር ማጤስን ማቆም በዚህ በሽታ የሚደረሰውን ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ያደርጋል። በዘር ግንድ ወይም በዘረ መል ላይ የሚፈጠር ለውጥ እንዲሁም የሰውነት የበሽታ መከላኪያ ሥርዓት የራስን የሰውነት ክፍሎች የማጥቃት ክስተት ወይም የጤና ችግር ለቡርገር በሽታ መፈጠር አጋላጭ ሆኔታዎች ናቸው ተብሎ ይታመናል።
በሽታው በብዛት በጎልማሳነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶችን እንደሚያጠቃ ይታወቃል።
ከቡርገር በሽታ ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል በእግር እና በእጅ ላይ የሚሰማ በተደጋጋሚ ግዜ የሚመጣ እና በራሱ የሚጠፋ ህመም ፣ በደም መልስ ቧንቧዎች ውስጥ የደም መርጋት መፈጠር ፣ የደም ሥር መገታተር ፣ ለቀዝቃዛ የአየር ሆኔታ በሚጋለጡበት ወቅት በጣቶች ላይ የቆዳ ለወጥ እና ህመም መከሰት እንዲሁም በእግር እና በእጅ ጣቶች ላይ የሚፈጠር ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ቁስለት መፈጠር ዋንኞቹ ናቸው።
የቡርገር በሽታ ከሌሎች የደም ቧንቧ ግድግዳ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ በሽታዎች ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች እና ስሜቶችን ስለሚያሳይ ከሌሎች በሽታዎች ለመለየት የሚረዱ ምረመራዎችን በማድረግ በሽታውን መለየት አስፈላጊ ይሆናል። ለቀዝቃዛ የአየር ሆኒታ መጋለጥን በመቀነስ እንዲሁም የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን በመጠቀም ህመሙን ማስታገስ ይቻላል።