14.1.3. የደክተስ አርተሪኦሰስ ማሳለፊያ አንደተከፈተ መቅረት (Patent Ductus Arteriosus/ PDA)
በልብ አፈጣጠር ሂደት እና ዕድገት ወቅት በሳንባዎች ውስጥ በሚፈጠረው ከፍተኛ መጠን ያለው ግፊት የተነሳ ደም በፑልሞናሪ አርተሪ በኩል ወደ ሳንባ ማለፍ አይችልም። ስለሆነም በፑልሞናሪ አርተሪ በኩል ከቀኝ ቬንትሪክል የሚረጨው ያልተጣራ ደም ወደ ሳንባ ከመግባት ይልቅ በደክተስ አርተሪኦሰስ ማሻገሪያ ወይም ቅያሽ በኩል አድርጎ ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ውስጥ የሚገባ ይሆናል። ከዚያም ይህ ደም በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በኩል ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ይረጫል።
ህጻኑ እንደተወለደ በሚተነፍስበት ወቅት ወደ ሳንባ በሚገባው አየር የተነሳ ሳንባዎች ስለሚለጠጡ እና በሳንባ ውስጥ የሚኖረው የግፊት መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሰለሚቀንስ በፑልሞናሪ አርተሪ በኩል ከቀኝ ቬንትሪክል የሚረጨው ደም በደክተስ አርተሪኦሰስ በኩል ከማለፍ ይልቅ በቀጥታ ወደ ሳንባዎች ውስጥ ይፈሳል። በፅንሱ ዕድገት ወቅት ደከተስ አርተሪኦሰስ እንደተከፈተ የሚቆየው በህፃኑ ደም ውስጥ የሚገኘው የኦክሰጂን መጠን ዝቅተኛ ስለሆነ እና በጽነሱ ደም ውሰጥ የሚገኘው የፕሮሰታግላንዲን ሆርሞን በከፍተኛ መጠን ላይ ስለሚገኝ ነው።
ህጻኑ ከተወለደ በኋላ በህጻኑ ደም ውስጥ በሚፈጠረው የኦክስጂን መጠን መጨመር እና ከእናትየው ወደ ፅንሱ የሚደርሰው የፕሮስታግላንዲን ሆርሞን መጠን መቋረጥ የተነሳ በደክተስ አርተሪኦሰስ ውስጥ የሚገኙ ጡንቻዎች ይኮማተራሉ። ይህም ሆኔታ የደክተስ አርተሪኦሰስ መሸጋገሪያ እንዲዘጋ እና ደክተስ አርተሪኦሰስ ወደ ሊጋመንተም አርተሪኦሰም (ligamentum Arteriosum) እንዲቀየር ያደርጋል። ህጻኑ ከተወለደ በኃላ በተለያዩ ምክንያቶች የደክተስ አርተሪኦሰስ በትክክል በመዘጋት ያልተጣራው ደም ከፑልሞናሪ አርተሪ ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ውሰጥ በመግባት የደክተስ አርተሪኦሰስ ማሳለፊያ አንደተከፈተ መቅረት (PDA) የጤና ችግር እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።
በፅንሱ ዕድገት ወቅት በፑልሞናሪ አርተሪ እና በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ መካከል የደም ዝውውር ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያደርገው ማሻገሪያ ወይም ደክተስ አርተሪሰስ ህጻኑ ከተወለድ በኋላም እንደተከፈተ እንዲቆይ ሊያደርጉ ከሚችሉ ሆኔታዎች መካከል ከውልደት ግዜ በፊት መወለድ (prematurity) ፣ በእርግዝና ወቅት እናትየው ለሩቤላ ወይም የጀርመን ኩፍኝ ኢንፌክሽን መጋለጥ ፣ በእርግዝና ወቅት የአልኮል መጠጥ መውሰድ ፣ ለእንፍርፍሬት በሽታ የሚስጡ መድኃኒቶች (የፌኒቲዮን /phenytoin መድኃኒት) ፣ ከፍተኛ መጠን ላለው የፕሮሰታግላንዲን ሆርሞን መጋለጥ እንዲሁም ፅንሱ በማህጸን ውስጥ እያለ ከፍተኛ ለሆነ የትንፋሽ ማጠር ወይም ለኦክስጂን እጥረት መጋለጥ እና በዘረ መል ወይም በክሮሞዞሞች ላይ ከሚፈጠር ለውጥ ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች (ዳውን ሲንድሮም) ዋንኞቹ ሆኔታዎች ናቸው።
ህጻኑ ከተወለደ በኃላ በተለያዩ ምክንያቶች የደክተስ አርተሪኦሰስ መዘጋት በማይከሰትበት ወይም የደክተስ አርተሪኦሰስ ማሳለፊያ አንደተከፈተ መቅረት የጤና ችግር በሚፈጠርበት ወቅት ከቀኝ ቬንትሪክል በፑልሞናሪ አርተሪ በኩል የሚረጨው ያልተጣራ ደም ወደ ሳንባ ከመግባት ይልቅ በደክተስ አርተሪኦስስ በኩል ወደ ትልቁ የደም ቅዳ ቧንቧ ውስጥ የሚገባ ይሆናል። ያልተጣራው ደም በደክተስ አርተሪኦሰሰስ በኩል ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ በመግባት እና ከግራ ቬንትሪክል ከሚረጨው የተጣራ ደም ጋር በመደባለቅ ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚደርስ ይሆናል። ይህ ዓይነት በልብ እና የደም ቧንቧ ሥርዓት አፈጣጠር ሂደት ወቀት ከሚፈጠር እክል የተነሳ ህፃኑ ከተወለደ በኃላ ከቀኝ ቬንተሪክል የሚረጨው ያልተጣራ ደም በቀጥታ ወደ ትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧ ውሰጥ እንዲገባ የሚያደርግ የጤና ችግር የደከተስ አርተሪኦሰስ እንደተከፈተ መቅረት (Patent Ductus Arteriosus) ተብሎ ይጠራል።
በደክተስ አርተሪኦሰስ እንደተከፈተ መቅረት የተነሳ የሚፈጠረው ግንኙነት መጠን ትንሽ በሚሆንበት ወቅት ከበሽታው ጋር በተገናኘ ምንም ዓይነት ምልክቶች እና ለውጦች ላይከሰት የሚችል ሲሆን መጠኑ ትልቅ በሚሆንበት ወቅት ግን የዕድገት መቀጨጭ እና ከልብ ድካም ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦች እንዲከሰቱ ሊያደርግ ይችላል።
በፑልሞናሪ አርተሪ እና በትልቁ ደም ቅዳ ቧንቧዎች መካከል የሚፈጠረው ግንኙነት በጣም ትንሽ በሚሆንበት ወቅት ያለምንም ህክምና በህጻኑ ላይ የሚከሰቱ ምልክቶችን እና ለውጦችን መከታተል አስፈላጊ ይሆናል። የግንኙነቱ መጠን ትልቅ በሚሆንበት ወቅት ወይም ከጤና ችግሩ ጋር የተገናኙ ምልክቶች እና ለውጦች በሚከሰቱበት ወቅት በቀዶ ጥገና የደክተስ አርተሪሰስ ማሻገሪያውን መድፈን ወይም መዝጋት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
ክወልደት ግዜ በፊት በሚወለዱ ህጻናት ላይ ሊከሰት የሚችለውን የደክተስ አርተሪኦሰስ አንደተከፈተ መቅረት እድል ለመቀነስ የፕሮስታግላንዲን ሆርሞን መመረትን እንዲቀንስ ለማድረግ የሚረዱ እንደ ኢንዶሜታሲን (Indomethacin) ወይም አይቡፕሮፊን (Ibuprofen) ያሉ መድኃኒቶችን መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
የደክተስ አርተሪኦሰስ እንደተከፈተ መቅረት የጤና ችግር ሳይታከም ለረጅም ግዜ በሚቆይበት ወቅት የልብ ድካም በሽታ ፣ በተደጋጋሚ በልብ የወሰጠኛ ክፍል ውስጥ የሚፈጠር እኢንፌክሽን ፣ የፑልሞናሪ አርተሪ የደም ግፊት መጠን መጨመር እና የኢዝንመንገር ሲንድሮም እና ሌሎች የጤና ችግሮችም እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል።