18.3. የልብ ጡንቻ መኮማተር እና መለጠጥ አለመቻል (Restrictive cardiomyopathy)
በልብ ጡንቻ ላይ ከሚፈጠር ጉዳት ጋር በተያያዘ የሚከሰት የልብ ጡንቻ መኮማተር እና መለጠጥ አለመቻልን የሚያስከትል የልብ የጤና ችግር የሚፈጠረው በተለያየ ምክንያት የቬንትሪክል ጡንቻ ባህሪ እና መዋቅራዊ አሰራር መለወጥ የተነሳ የቬንትሪክል ጡንቻ በሚፈለገው መጠን መኮማተር እና መለጠጥ አለመቻል ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ነው። የልብ ጡንቻ መኮማተር እና መለጠጥ አለመቻል የሚያስከትል የልብ የጤና ችግር ብዙሁን ግዜ የሚከሰተው በልብ ወይም በቬንትሪክል ጡንቻ ውስጥ በመከማቸት የቬንትሪክል ጡንቻን ተግባር በሚቀነሱ ሆኔታዎች ነው። ይህም ማለት ይህ የጤና ችግር ብዙሁን ግዜ የሚከሰተው ከሌሎች የጤና ችግሮች ጋር በተገናኘ ነው።
በቬንትሪክል ጡንቻ ውስጥ በመከማቸት በቬንትሪክል ጡንቻ ተግባር ላይ ተጽህኖ ከሚያሳድሩ የጤና ችግሮች ወይም ሆኔታዎች መካከል ሳርኮይድኦሲስ (Sarcoidosis) ፣ በሰውነት ወሰጥ በመጠን የሚጨምሩ ፕሮቲኖች በልብ ጡንቻ ውስጥ መከማቸት የተነሳ የሚፈጠር የጤና ችግር ወይም አማይሎይዶሲስ (amyloidosis) ፣ በሰውነት ክፍሎች ወስጥ የሚፈጠር የብረት መከማቸት ወይም ኢሞክሮማቶሲስ (hemochromatosis) እና የሴሎች ያለቆጥጥር መራባት እና መብዛት (neoplasia) ዋንኞቹ ሆኔታዎች ናቸው። በተጨማሪም ሌሎች በልብ ጡንቻ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ እንደ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በተለይም የቆዳ በጠባሳ መተካትን የሚያሰከትል የጤና ችግር ወይም ሰክለሮደርማ (scleroderma) እና በሴሎች ላይ የከፋ ጉዳት ለሚያሰከትል ጨረር (radiation) መጋለጥ ያሉ ሆኔታዎች የልብ ጡንቻ መኮማተር እና መለጠጥ አለመቻል የሚያስከትል የልብ የጤና ችግር እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።
ከዚህ ዓይነት የልብ ጡንቻ የጤና ችግር ጋር በተገናኘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ምልክቶች እና ለውጦች መካከል የትንፋሽ ማጠር ፣ ከትንፋሽ ማጠር የተነሳ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻል እና የድካም ስሜት መሰማት በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ምልክቶች እና ለውጦች ናቸው። በተጨማሪም በአንገት አካባቢ የሚገኙ የደም ቧንቧዎች መገታተር ፣ የሰውነት ዕብጠት ፣ የጉበት መጠን መጨመር ፣ በሆድ ውስጥ የሚገኘው የፈሳሽ መጠን መጨመር እና ከልብ ምት ጋር ጤነኛ ያለሆነ ድምጽ መስማት ሊከሰት ይችላል።
ይህ የጤና ችግር መከሰቱን ለማወቅ ከሚደርጉ የምርመራ መንገዶች መካከል በደረት ራጅ ምርመራ የልብ መጠን መጨመር እና የፑልሞናሪ የደም ቧንቧዎች መስፋትን ማየት ይቻላል። የኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራን በመጠቀም የልብ ጡንቻ መወፈርን እና የልብ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴን መዛባት መለየት ይቻላል።
በኢኮካርዲዮግራም ምርመራ ደግሞ የሁሉም የልብ ክፍሉች መወፈርን ማየት የሚቻል ሲሆን በካርዲያክ ካቴተራይዜሽን ( cardiac Catheterization) ምርመራ ደግሞ በግራ እና በቀኝ ቬንትሪክል ውስጥ የሚገኘው የግፊት መጠን መጨመርን ማወቅ ይቻላል። የልብ ጡንቻ መኮማተር እና መለጠጥ አለመቻል የሚያስከትል የልብ የጤና ችግርን በሚገባው መልኩ ማከም በጣም አስቸጋሪ ሲሆን በዚህ የጤና ችግር የተጠቁ በሽተኞች ከልብ ድካም እና የልብ ምት መዛባት ጋር በተገናኘ ሀይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።